ጉቴሬዝ የጸጥታው ምክርቤትን ለማስጠንቀቅ የተጠቀሙት “አንቀጽ 99” ምን ይላል?
የተመድ ዋና ጸሃፊ የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ ጉዳይ ፈጣን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንዲያሳልፍ አሳስበዋል
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የቀረቡ የውሳኔ ሃሳቦች በአሜሪካ ውድቅ መደረጋቸው ይታወሳል
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እምብዛም ተጠቅመውበት የማያውቁትን ስልጣናቸውን ለጋዛ አውለውታል።
በድርጅቱ ማቋቋሚያ ቻርተር አንቀጽ 99 ላይ ዋና ጸሃፊው አለማቀፍ የሰላምና ደህንነት ስጋት ተደቅኗል ብለው ሲያምኑ የጸጥታው ምክርቤትን የማሳሰብ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።
“አለማቀፉ ማህበረሰብ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እየተባባሰ እንዳይሄድ የትኛውንም አይነት ጫና የማድረግ ሃላፊነት አለበት“ ያሉት ጉቴሬዝ፥ 15 አባላት ላሉት የጸጥታው ምክርቤት ፕሬዝዳንት ደብዳቤ አስገብተዋል።
ምክርቤቱ በአፋጣኝ ተሰብስቦ በጋዛ እየተባባሰ የመጣውን ሰብአዊ ቀውስ የሚገታ ውሳኔ እንዲያሳልፍም ነው ያሳሰቡት።
የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሬክ፥ ዋና ጸሃፊው በዚህ ሳምንት በጸጥታው ምክርቤት ስብሰባ ተገኝተው ምክርቤቱ ሁለት ወራት ለደፈነው ጦርነት አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባሉ ብለዋል።
የጉቴሬዝን የማሳሰቢያ ደብዳቤ ተከትሎም የጸጥታው ምክርቤት አባል የሆነችው አረብ ኤምሬትስ በጋዛ የሰብአዊ ተኩስ አቁም እንዲደረስ ረቂቃ የውሳኔ ሃሳብ ለምክርቤቱ ማስገባቷን ገልጻለች።
በጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የቀረቡ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳቦች ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ባላት አሜሪካ ውድቅ መደረጋቸው የሚታወስ ነው።
ዋሽንግተን የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳቡ የፍልስጤሙን ሃማስ የመዘጋጃ እድሜ ይጨምርለታል በሚል ነው የውሳኔ ሃሳቦቹን የተቃወመችው።
ምክርቤቱ የተመድ ዋና ጸሃፊው በአንቀጽ 99 የተሰጣቸውን ስልጣን ተጠቅመው ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ይደረስ ሃሳብ ተቀብሎት ከጸደቀ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ የመጣልና የውጭ ሀገር ወታደሮችን እስከማስገባት የደረስ እርምጃ መውሰድ ይችላል።
የእስራኤል ወዳጅ አሜሪካ ግን ድጋፍ ትሰጠዋለች ተብሎ አይጠበቅም ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
በመንግስታቱ ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኢርዳንም የጉቴሬዝን እርምጃ “ከሞራል ዝቅ ያለ እና ከእስራኤል በተጻራሪ የቆመ” ሲሉ ተቃውመውታል።
የዋና ጸሃፊው የተኩስ አቁም ጥሪ ሃማስ በጋዛ የሽብር ተግባሩን እንዲቀጥል እንደመፈለግ የሚታይ ነው ሲሉም ጉቴሬዝን ወቅሰዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከጥቅምት 18 2023 ጀምሮ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም እያቀረቡት የሚገኙት ጥሪ ከእስራኤል መንግስት ተደጋጋሚ ትችት አስከትሎባቸዋል።