አሜሪካ በዌስትባንክ በሚገኙ “ጽንፈኛ” እስራኤላውያን ላይ የጉዞ ክልከላ ጣለች
የቪዛ ማዕቀቡ በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት በሚያደርሱ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ላይ ነው የተጣለው
ዋሽንግተን የእስራኤል መንግስት በዌስትባንክ የተፈጠረውን ሁከት ማስቆም አልቻለም በሚል ወቅሳለች
አሜሪካ እስራኤል በሃይል በያዘቻት ዌስትባንክ በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት በሚያደርሱ የእስራኤል ሰፋሪዎች ላይ የቪዛ ክልከላ ማዕቀብ ጣለች።
ክልከላው እስራኤላውያን ያለቪዛ አሜሪካ እንዲገቡ ከተፈቀደ ከአንድ ወር በኋላ ነው የተጣለው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንትኒ ብሊንከን የጉዞ ክልከላው በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት እያደረሱ በሚገኙ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
አሜሪካ ከመግባት የሚያግደው የጉዞ ማዕቀብ በዌስትባንኩ ሁከት ተሳትፎ ያላቸውን ፍልስጤማውያን እንደሚያካትትም ነው የገለጹት።
- እስራኤል ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከባድ የተባለ ውጊያ ማካሄዷን ገለጸች
- አይሲሲ የእስራኤል ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እየመረመረ መሆኑን ገለጸ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር፥ ክልከላው “በደርዘን በሚቆጠሩ ጽንፈኛ” እስራኤላውያን እና ቤተሰቦቻቸው ላይ መጣሉን ቢጠቅሱም እገዳው የተላለፈባቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ይፋ አላደረጉም።
በአሜሪካ ውሳኔ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት፥ “በጽንፈኛ ሃይሎች የሚፈጠር ሁከትን ልናወግዝ ይገባል” ብለዋል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለቴል አቪቭ የማያቋርጥ ድጋፍ እያደረገች የምትገኘው ዋሽንግተን የእስራኤል መንግስት የዌስትባንኩን ሁከት ማረጋጋት አለመቻሉ ስጋት ፈጥሮባታል ተብሏል።
እስራኤላውያኑ ሰፋሪዎች የጋዛውን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የፍልስጤማውያንን መሬት ለመያዝ እየተጠቀሙበት መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ፍልስጤማውያን ተናግረዋል።
በ1967ቱ የአረብና እስራኤል ጦርነት በኋላ እስራኤል ዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌምን ከተቆጣጠረች በኋላ ከ700 ሺህ በላይ አይሁዳውያንን ከ250 በላይ በሚሆኑ የሰፈራ መንደሮች አስፍራለች።
አለማቀፉ ማህበረሰብ ይህ የቴል አቪቭ የሰፈራ ፕሮግራም ከአለማቀፉ ህግ የሚጣረስ ነው በሚል ቢቃወሙትም እስራኤል እና አሜሪካ የአተረጓጎም ልዩነት አለ በሚል ሲከራከሩ ይታያል።
ከጥቅምት 7ቱ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት በኋላ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት መጨመሩን የሚያነሳው የመንግስታቱ ድርጅት፥ እስካሁን በፍልጤማውያን ላይ የተሰነዘሩ 314 ጥቃቶች መመዝገባቸውን ገልጿል።
አራት እስራኤላውያንም በዌስትባንክ በፍልስጤማውያን መገደላቸውን በመጥቀስ እስራኤል ሁከቱን ማርገብ አልቻለችም ሲል መውቀሱን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።