አሜሪካ በጸጥታው ምክር ቤት በጋዛ ጦርነቱ እንዲቀጥል ድምጽ ሰጠች
ብራዚል በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍን ለማድረስ ጦርነቱ ጋብ እንዲል ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ በዋሽንግተን ተቃውሞ ሳይጸድቅ ቀርቷል
አሜሪካ የእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት እንዲቆም እንደምትፈልግ ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል
አሜሪካ በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የተኩስ አቁም እንዲደረስ እንደማትፈልግ በጸጥታው ምክርቤት ተቃውሞዋን በማሰማት አሳይታለች።
በብራዚል የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ቻይና፣ ፈረንሳይ እና ኤምሬትስን ጨምሮ 12 ሀገራት ደግፈውታል፤ ሩሲያ እና ብሪታንያ ደግሞ ድምጻቸውን ባለመስጠት (በተአቅቦ) አልፈውታል።
የውሳኔ ሃሳቡን በብቸኝነት የተቃወሙት በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ናቸው።
አሜሪካ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እንዲቆም እንደምትፈልግ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይሁን እንጂ ዋሽንግተን ከዛሬው የጸጥታው ምክርቤት ጦርነቱ ይቀጥል ግልጽ አቋሟ በፊትም ወገንተኝነቷን በገሃድ አሳይታለች።
የፍልስጤሙን ሃማስ በሽብር የፈረጀችው አሜሪካ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረገች ነው።
ከ2 ሺህ በላይ ወታደሮችን ወደ ቴል አቪቭ ከመላክ ባሻገርም አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቧን ወደ እስራኤል ማስጠጋቷ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ ቴል አቪቭ መግባታቸውም የአጋርነታቸው ማሳያ ነው።
ባይደን ከግብጽ እና ዮርዳኖስ መሪዎች ጋር ከጋዛ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ሰብአዊ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ጉዳይ ለመምከር ቀጠሮ መያዛቸው ተነግሮ በኋላ ቢሰረዝም በጸጥታው ምክር ቤት ሀገራቸው ያንጸባረቀችው አቋም ከቀደመ መግለጫቸው ተቃርኖ ታይቷል።
ከዚህ ቀደም በጸጥታው ምክርቤት ለእስራኤል ዘብ በመቆም የምትታወቀው አሜሪካ በጋዛ ሰርጥ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረግኩ ነው በሚል በብራዚል የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አድርጋዋለች።
ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ስላላት 193 አባል ያለው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቃለች።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ በበኩላቸው በጋዛ ሰርጥ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ተደርሶ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲሰራጭ እና የታገቱ ሰዎች እንዲለቀቁ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።