የተመድ ዋና ጸሃፊ የሩሲያ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንቶችን በግንባር ሊያገኙ ነው
ከሩሲያ መልስ በዚያው ወደ ዩክሬን አቅንተው ከፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜለንስኪን ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመጪው ማክሰኞ ወደ ሩሲያ አቅንተው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ያገኛሉ ተብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመጪው ሳምንት የሩሲያ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንቶችን በግንባር አግኝተው ሊመክሩ ነው ተባለ፡፡
ጉቴሬዝ በመጪው ማክሰኞ ወደ ሞስኮ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚወያዩ የዋና ጸሃፊው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ጉቴሬዝ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበት ጦርነት ሊቆም በሚችልበት ዙሪያ ለመምከር ነው ወደ ሞስኮው የሚያቀኑት፡፡
በዚያው ወደ ዩክሬን ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜለንስኪን ጋር ይወያያሉም ተብሏል፡፡
ጉቴሬዝ የሩሲያ ድርጊት ዓለም አቀፍ ህግጋትን የሚጥስ እና ከተመድ ቻርተርም የሚቃረን ነው በሚል ከአሁን ቀደም ተናግረው ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት ፑቲንን በስልክ አግኝተው ለማውራት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ሆኖም በንግግሩ ደስተኛ እንዳይደሉ የተነገረላቸው ፑቲን ጉቴሬዝን ለማናገርም ሆነ ስልካቸውን ለማንሳት አልፈቀዱም፡፡
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪንም እምብዛም አግኝተዋቸው አያውቁም፡፡ ጦርነቱን ተከትሎ አንድ ጊዜ ብቻ ነው በስልክ ያገኟቸው፡፡
በመሆኑም ጉቴሬዝ የሃገራቱን መሪዎች በግንባር አግኝተው ለማነጋጋር ከሰሞኑ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበርም ተነግሯል፡፡ ደብዳቤው በጦርነቱ ምክንያት የጸጥታው ምክር ቤት መስማማት አለመቻሉን ተከትሎ የተጻፈ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባል የሆነችው ቻይና ልክ እንደነ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ሁሉ የሩሲያን ድርጊት ለማውገዝ አልፈለገችም፡፡
ዋና ጸሃፊው 2 ወራትን ሊደፍን የቀናት እድሜ ብቻ የቀረው ጦርነት እንዲቆም ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ በዚህ የበዓል ሰሞን እንኳን ተኩስ እንዲያቆሙ ጠይቀውም ነበር፡፡ ሆኖም ጥያቄው አልተሳካም፡፡ ጦርነቱም ቀጥሏል፡፡ 12 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ተፈናቅለዋልም ነው የሚባለው፡፡