ፔፕ ጋርዲዮላ ማንቸስተር ሲቲ የመጨረሻው የሚያሰለጥኑት ቡድን እንደሚሆን ተናገሩ
አሰልጣኙ ከ11 አመት የሲቲ የአሰልጣኝነት ቆይታ በኋላ ከክለብ አሰልጣኝነት ራሴን አገላለሁ ብለዋል
ከእንግሊዙ ክለብ ጋር 6 የሊጉን ዋንጫ ያነሱት ፔፕ 3 ጊዜ ምርጥ የክለብ አሰልጣኝ በመሆን ተመርጠዋል
ስፔናዊ የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርድዮላ የክለብ አሰልጣኝነት ዘመናቸው በእንግሊዙ ቡድን ሲቲ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡
ከ2016 ጀምሮ ማንችስተር ሲቲን ሲያሰለጥኑ የቆዩት ጋርድዮላ በቡድኑ በነበራቸው ቆይታ 15 ትላልቅ ዋንጫዎችን ማሳካት ችለዋል፡፡
በቅርቡ እስከ 2027 ድረስ የሚያቆያቸውን የወል ማራዘሚያ ኮንትራታቸውን የፈረሙ ሲሆን ውላቸው ሲጠናቀቅ አጠቃላይ በሲቲ ቤት የሚኖራቸው ቆይታ 11 አመት ይሞላል፡፡
ጋርድዮላ ምንም እንኳን ከክለብ አሰልጣኝነት ራሳቸውን ቢያገሉም የብሔራዊ ቡድኖችን ማሰለጥን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ከስፔን የዩትዩብ የስፖርት ፕሮግራም ቻናል ጋር በነበራቸው ቆይታ "የክለብ ቆይታየ በማንችስተር ሲቲ እንዲጠናቀቅ አቅጃለሁ፤ አሁን በምገኝበት ሁኔታ አዲስ ቡድን ተቀብሎ ለማስልጠን ሞራሉ የለኝም፤ ነገር ግን ወደ ፊት ከብሔራዊ ቡድኖች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን የማጤንበት እድል ይኖራል" ነው ያሉት፡፡
የ53 አመቱ አሰልጣኝ ስኬታማ ከሚባሉ ስፔናውያን የክለብ አሰልጣኞች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
በባርሴሎና ሁለት ጊዜ ፣ በማንችስተር ሲቲ ደግሞ አንድ ጊዜ በአጠቃላይ ሶስት ምርጥ የክለብ አሰልጣኝ እውቅናዎችን አግኝተዋል፡፡
በተጨማሪም በባርሴሎና ሁለት ጊዜ በሲቲ 1 ጊዜ ሶስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችንም ማሳካት ችለዋል፡፡
የአራት ጊዜ የፊፋ የክለቦች የአለም ዋንጫ አሸናፊው አሰልጣኝ ከማንችስተር ሲቲ ጋር 6 የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ዋንጫ ክብርን ተቀዳጅተዋል፡፡
በቀደሙት አመታት የሚታወቅበትን ውጤታማነት ማስቀጠል የተሳነው የእንግሊዙ ቡድን ወደ ተፎካካሪነት ለመመለስ ጥረቶችን እያደረገ ቢገኝም ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖታል በሚል እየተተቸ ነው፡፡
ካለፉት 9 ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ የቻለው ሲቲ ዛሬ ምሽት በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ከጣሊያኑ ሀያል ቡድን ጁቬንትስ ጋር ይገናኛል፡፡
በሻምፒዮንስ ሊግ እየተሳተፉ ከሚገኙ 36 ቡድኖች ወደ 16ተኛው ዙር ለማለፍ 8 ምርጥ ቡድኖችን ለመለየት እየተደረገ በሚገኝው ፊክክር ሲቲ በ20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ከስድስት ጨዋታዎች ተከታታይ ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ በሳለፍነው ሳምንት ኖቲንግሀም ፎረስትን 3 ለዜሮ ያሸነፈ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ከክርስቲያል ፓላስ ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል፡፡
በመጪው እሁድ ደግሞ ከከተማ ተቀናቃኙ ማንችስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡