ፑቲን በማዕከላዊ እስያው ስብሰባ ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናከሩ
ሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ስምምነት ለመፈራረም መቃረባቸውን ፔዝሽኪያን ተናግረዋል።
ፑቲን የኢራኑ ፕሬዝደንት ፔዝሽኪያን በሩሲያ ይፋዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸው እና የኢራኑ መሪም መቀበላቸው ተገልጿል
ፑቲን በማዕከላዊ እስያው ስብሰባ ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናከሩ።
የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከኢራኑ አቻቸው ፕሬዝደንት መሱድ ፔዝሺኪያን ጋር በትናንትናው እለት በቱርኬሚስታን ተገናኝተው መወያየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን እና እያደገ የመጣውን መልካም ግንኙነት ማድነቃቸውን እና በአለምአቀፋዊ ጉዳዮች ተመሳሳይ አቋም ማንጸባረቃቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ከአሜሪካ እና ከአውሮፓውያን ጋር አለመግባባት ውስጥ የገቡት ፑቲን በምስራቅ እና ደቡብ ካለው የአለም ክፍል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ትዕቢተኛ እና የራሳቸውን ፍላጎት የሚያራምዱ ሲሉ የገለጿቸውን ምዕራባውያን መታገል ይፈልጋሉ።
የብሪክስን ስብሰባ ከጥቅምት 22-24 በካዛን የምታስተናግደው ሀገር ፕሬዝደንት የሆኑት ፑቲን የኢራኑ ፕሬዝደንት ፔዝሽኪያን በሩሲያ ይፋዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውን እና የኢራኑ መሪም መቀበላቸውን የሩሲያው ሪያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
"በባህል እና በኢኮኖሚ ያለን ግንኙነት በየቀኑ እያደገ ነው" ሲሉ ፔዝሽኪያን መናገራቸውን የኢራኑ አይአርኤንኤ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ፔዝሽኪያን አክለውም እንደገለጹት "የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ፍላጎት ስላላቸው እያደገ ያለው የሩሲያ እና ኢራን ግንኙነት መፍጠን እና መጠናከር አለበት" ብለዋል። የሩሲያው ታስ እንደዘገበው ሁለቱ ሀገራት በብዙ ዘርፎች ለመተባበር ተስማምተዋል።
"ከሩሲያው ፕሬዝደንት ጋር አንድ ሰአት የፈጀ ውይይት አድርገናል። በተስማማንባቸው ጉዳዮች ላይ በድጋሚ ተነጋግረናል"ሲሉ ፔዝሽኪያን መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ኢራን ምዕራባውያን የጣሉባትን ማዕቀብ ለመቋቋም ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ፔዝሽኪያኒ ባለፈው ወር ተናግረው ነበር። ሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ስምምነት ለመፈራረም መቃረባቸውን እና ይህ ስምምነት በዚህ ወር መጨረሻ በሩሲያ በሚካሄደው የብሪክስ ስብሰባ ወቅት ይጠናቀቃል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ፔዝሽኪያን ተናግረዋል።
ሩሲያ ከኢራን ጋር የሚደረገው ግንኙነት በሁሉም መስክ እየሰፋ ነው ብላለች።
ከምዕራባውያን ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባችው ሩሲያ ተገዳዳሪ አዲስ የአለም ስርአት እንዲፈጠር ጥረት እያደረገች ነው።