መንግስቴን ያለአግባብ የሚገስጸው አለምአቀፉ ማህበረሰብ ህወሃትን በጥብቅ ማስጠንቀቅ አልቻለም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
አሜሪካ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ በባለስልጣናት ላይ ማእቀብ እጥላለሁ ብላለች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የህወሃትን ድርጊት በመቃወም ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግልጽ ደብዳቤ ጻፉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ያላግባብ በመንግስታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ የሚገስጸው አለምአቀፉ ማህበረስብ እንዳለመታደል ሆኖ ህወሃትን በተመሳሳይ መልኩ በግልጽና በጥብቅ ማስጠንቀቅ አልቻለም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስሩ ይህን ያሉት በዛሬው እለት የህወሃትን ድርጊቶች በመቃወም ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ነው፡፡
- ፕሬዝዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ማእቀብ እንዲጣል ትእዛዝ አስተላለፉ
- የአማራ ክልል መንግስት ህወሃት በሰነዘረው ጥቃት በክልሉ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል አለ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በደብዳቤያቸው የኢትዮጵያ መንግስት በህወሃት ምክንያት የተፈጠረውን የሰብአዊ ፍላጎት ችግር ለማረጋጋት ያደረገው ጥረት በልተገባ መልኩ ተተርጉሟል ብለዋል፡፡
ይህ ያልተገባ ጫና ወይንም ፍትሃዊ ያለመሆን ተግባር የመነጨው መንግስት በትግራይ ክልል ባካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻዎች የነበሩ ክስተቶችን በማዛባት የመጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የረጅም ጊዜ አጋር የሆነችው አሜሪካ ኢትዮጵያን የሚጻረር ፖሊሲ ማራመዷእንዳስገረማቸውና ጉዳዩ ከሰብአዊ ጉዳይ ያለፈ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ይህን ደብዳቤ በምጽፍበት ጊዜ ሴቶችን፤ህጻናቶችንና ተጋላጭ ጨምሮ ንጽሃን በአፋርና በአማራ ክልል በሀይል ተፈናቅለዋል፤ ኑሯቸው ተመስቃቅሏል፤የቤተሰብ አባሎቻቸው ተገድለዋል እንዲሁም ንብረታቸውና አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች ሆንተብሎ በህወሃት ወድመዋል” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
“በትግራይ ክልልም ልጆቻችን በሽብር በተፈረጀው ህወሓት ለጦርነት እየተማገዱ” ነው በማለት ለባይደን ባጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ አለምአቀፍ ህግን የጣሰ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፋርና አማራ በክልል በህወሃት ተሰቃይተው የፈናቀሉ ሴቶችን ጩኸት አለምአቀፍ ማህበረስብ ሊሰማ አልፈለገም ብለዋል፡፡
“በደብዳቤያቸው በብዙ የአለም ክፍሎች ያሉ ሀገራዊ ፤ቀጣናዊና አለምአቀፍ የደህንነት ስጋቶች የአሜሪካ ቁልፍ ብሄራዊ ፍላጎት ሆነው ሳለ፤ የአሜሪካ ሆምላንድ ሴኩሪቲ በ1980ዎቹ በአሸባሪነት በፈረጀው ህወሃት ላይ ለምን ጠንካራ አቋም አላራመደም የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ፡፡
የትግራይን ክልል በሚያስደደረውና በፌደራል መንግስት መካከል ባለፈው አመት ጥቅምት ወር የተቀሰቀሰው ግጭት 11 ወራት አስቆጥሯል፤ እስካሁንም መቆም አልቻለም፡፡ ግጭቱ የተጀመረው የህወሃት ሃይሎች በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከለትሎ ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት ግጭቱን በውይይት ለመፍታት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ክትግራይ ክልል ቢያስወጣም፤ ግጭቱ ሊቆም አልቻለም፡፡ በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ወደ አፋርና አማራ ክልል ሊስፋፋ ችሏል፡፡
የፌራል መንግስት፤ ተኩስ አቁም የተፈለገውን ተኩስ አቁም ባለማምጣቱ፤ መከላከያና የክልል ልዩ ኃይሎች በህወሃት ሃይሎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አዞ፤ጦርነቱ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ አለምአቀፍ ማህበረሰብ የፌደራል መንግትና ህወሓት ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ጫና በማሳደር ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ከሚሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በግለሰቦች ላይ ማእቀብ መጣል የሚያስችል ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳት ባይደን ማእቀቡን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ፤ በሰሜን እትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሰብአዊ ድጋፍ እንዲፈልጉ እና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሁለቱ አካለት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ፣ አሁን ላለው ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣ፣የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ግዛት ለቆ እንዲወጣ እና አንድነቷ የተጠበቀ እና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት እንደሚደግፈውም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።