ኬንያ የታክስ ጭማሪ ተቃውሞን ተከትሎ ትምህርት ቤቶችን ዘጋች
በሀገሪቱ ሁለት ዙር የተቃውሞ ሰልፎች ወደ ሁከት አምርተው ቢያንስ 15 ሰዎች ተገድለዋል
የኬንያ መንግስት የጣለው የነዳጅ እና የመኖሪያ ቤት ቀረጥ እያደገ የመጣውን የብድር ጫና ለመቋቋምና ለስራ ፈጠራ ነው ብሏል
የኬንያ መንግስት በዋና ከተማው እና በሌሎች ሁለት አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ዘግቷል።
በኬንያ ለሦስተኛ ቀን የኑሮ ውድነትን በመቃወም ሰልፎችን መደረጋቸውን ተከትሎ ነው ትምህርት የተዘጋው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሁለት ዙር የተቃውሞ ሰልፎች ወደ ሁከት አምርተው፤ ቢያንስ 15 ሰዎች ተገድለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ታስረዋል።
የኬንያ ተቃዋሚዎች ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ የድሆችን ጥቅም ለማስከበር የገቡትን ቃል አፍርሰዋል በሚል ሰልፉን ጠርተዋል።
መንግስት ያደረገው የግብር ጭማሪ መሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።
በዓመት 200 ቢሊዮን ሽልንግ (1.4 ቢሊዮን ዶላር) ይሰበስባል ተብሎ የሚጠበቀው የነዳጅ እና የመኖሪያ ቤት ቀረጥ፤ እያደገ የመጣውን የብድር ጫና ለመቋቋም እና ለስራ ፈጠራ ውጥኖች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
አብያተ ክርስቲያናት እና የሲቪል መብት ተሟጋቾች ፕሬዝዳንት ሩቶ እና አንጋፋው የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ እና ተቃውሞውን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
ኦዲንጋ ያለፉትን አምስት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ማሸነፍ ባይችሉም፤ ከዚህ ቀደም በሁከትና ብጥብጥ ወቅት በስምምነት ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎችን ማግኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።