የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሄነሪ ስልጣን ለመልቀቅ ተስማሙ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጃማይካ ከአካባቢው ሀገራት መሪዎች ከመከሩ በኋላ የሰጡት መግለጫ የታጠቁ ሃይሎችን ማስደሰቱ ተነግሯል

የሄይቲ ወንበዴ ቡድኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ካልለቀቁ የእርስ በርስ ጦርነት እንደሚጀመር ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል
የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሄነሪ ስልጣን ለመልቀቅ ተስማሙ።
መዲናዋን ፖርት ኦው ፕሪንስ ተቆጣጥረው 4 ሺህ የሚጠጉ እስረኞችን ያስለቀቁ የወሮበላ ቡድኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
የጸጥታ ሁኔታው ወደ ሀገራቸው መግባት ሳያስችላቸው በፖርቶ ሪኮ ደሴት ለመቀመጥ የተገደዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሄነሪ ትናንት በጃማይካ ከአካባቢው ሀገራት መሪዎች ጋር መክረዋል።
ከምክክሩ በኋላም ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ይፋ ያደረጉበትን የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሀምሌ ወር 2021 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆቭኔል ሞይሴ ከተገደሉ በኋላ በጊዜያዊነት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሄንሪ፥ ምርጫ እንዲካሄድ አለማድረጋቸውና የወንበዴ ቡድኖች እንዳሻቸው እንዲሆኑ መፈቃደቸው በዜጎቻቸው ሲያስተቻቸው መቆየቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
መዲናዋን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የስአት እላፊ እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም የጸጥታ ሁኔታው መረጋጋት አላሳየም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሄነሪ በጃማይካው ውይይት ስልጣን እንደሚለቁ ማሳወቃቸውን ተከትሎም የታጣቂ ቡድኖች ደስታቸውን እየገለጹ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
“ከ40 በላይ የፖሊስ ጣቢያዎች ወድመዋል፤ ወታደሮችም ጥቂትና መሳሪያ ያልታጠቁ ናቸው፤ ይህም የወሮበላ ቡድኖች መዲናዋን እንዲቆጣጠሩ አድርጓቸዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከባድ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
በጃማይካው ምክክር ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመርጥና ሰባት አባላት ያሉት የሽግግር ምክርቤት ይቋቋማል የተባለ ሲሆን፥ ምክርቤቱ በካሪቢያኗ ሀገር ከ2016 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሄነሪ ኬንያ በወንበዴ ቡድኖቹ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ እንድታግዝ በናይሮቢ ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መምኸራቸው ጫናውን እንዳበዛባቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ መፈለጓን በተዘዋዋሪ ያሳየችው አሜሪካ ናይሮቢ ለምትመራው የተመድ ተሎዕኮ ተጨማሪ 100 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።