በጋዛ ከ10 ሰዎች ዘጠኙ በቀን አንዴ እንኳን ምግብ እያገኙ አይደለም - ተመድ
የጦርነቱ ዳግም ማገርሸት ለረሃብ የሚጋለጡ ፍልስጤማውያንን ቁጥር እንደሚያሻቅበውም ድርጅቱ ገልጿል
የእርዳታ ድርጅቶች አሜሪካ በጋዛ ተኩስ እንዲቀጥል መፈለጓ ሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰው ነው ብለዋል
ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን የጋዛ ሰርጥ ነዋሪዎች ግማሹ ለረሃብ መጋለጣቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አስታውቋል።
በበርካታ አካባቢዎ ከ10 ፍልስጤማውያን ውስጥ ዘጠኙ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ እንደማይችሉም ነው በተመድ የአለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ካርል ስኳ።
በጋዛ የተኩስ አቁም ተደርሶ በነበረበት ወቅት በየቀኑ ከ200 በላይ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እየገቡ እንደነበር ያወሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፥ ጦርነቱ ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ የሰብአዊ ድጋፍ ማስገባት ከባድ መሆኑን አብራርተዋል።
በጋዛ ጉብኝት ሲያደርጉ በረሃብ የሚሰቃዩ በርካታ ፍልስጤማውያንን መመልከታቸውን የሚያነሱት ካርል ስኳ፥ የራፋህ የድንበር መተላለፊያ ተከፍቶ ሰብአዊ ድጋፍ በፍጥነት እንዲገባ ጠይቀዋል።
በጋዛ ዳግም ያገረሸው ጦርነት ግን የእርዳታ ቁሳቁሶችን ማስገባት የማያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን በማንሳትም የከፋ ሰብአዊ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት ጦርነቱ እንዲቆም ነው ያሳሰቡት።
እስራኤል በበኩሏ በሃማስ ላይ የምወስደውን እርምጃ አላቆምም ብላለች።
የሀገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ሪቻርድ ሄችት “ምንም እንኳን የንጹሃን ህልፈት እና ሰቆቃ ቢያመንም ሌላ ምርጫ የለንም” በሚል ጦርነቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረቡ የሚገኙት አለማቀፍ ድርጅቶች አሜሪካ በጸጥታው ምክርቤት የቀረበውን የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ማድረጓ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ የቃኘ አይደለም በሚል ተችተዋል።
የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስም ዋሽንግተን በጦር ወንጀል ተሳትፎ እያደረገች ነው በሚል ውሳኔውን አትብቀው ተቃውመውታል።
በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሮበርት ውድ ግን የውሳኔ ሃሳቡ ሃማስ በጥቅምት 7 2023 የፈጸመውን ድርጊት እንዲደግም የሚፈቅድ ነው በሚል ተከላክለዋል።
እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ጥቃት ንጹሃንን እንዲጠብቅ የይስሙላ መግለጫ የምታወጣው አሜሪካ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከ2 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ግድ እንደማይሰጣት አሳይታለች።
የባይደን አስተዳደር ከ106 ሚሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የታንክ ጥይቶች ለእስራኤል በአስቸኳይ ለመሸጥ የኮንግረንሱን ይሁንታ ሳይጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉንም ቢቢሲ ዘግቧል።
የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 17 ሺህ 700 ደርሷል፤ ከሟቾቹ ውስጥ 7 ሺህ ያህሉ ህጻናት ናቸው።