የአለም ጤና ድርጅት ከደቡብ ጋዛ ከሚገኙ መጋዘኖች መድሃኒቱን እንዲያዛውር መገደዱን ገለጸ
የድርጅቱ ባለስልጣናት በጋዛ የንጹህ መጠጥ ውሃ አለመኖሩ ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ተናግረዋል
ተኩስ አቁም ከተጣሰ በኋላ 800 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል
የአለም ጤና ድርጅት ከደቡብ ጋዛ ከሚገኙ መጋዘኖች መድሃኒቱን እንዲያዛውር መገደዱን ገለጸ።
የአለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በሚገኙ መጋዘኖች የነበረውን መድሃኒት በ24 ሰአት ውስጥ እንዲያዛውር አስጠንቅቃዋለች።
እስራኤል ድርጅቱ መድሃኒቱን እንዲያዛውር ያስጠነቀቀችው በጋዛ የምታደርገው የእግረኛ ጦር ዘመቻ ቦታው ዝግ ይሆናል በሚል ምክንያት ነው ተብሏል።
የድርጅቱ ዳሬክተር ጀነራል ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኤክስ ገጻቸው እስራኤል ያስተላለፈችውን ማስጠንቀቂያ እንድታነሳ እና ንጹሃን ለመከላከል ሁሉንም አይነት እርምጃ እንድትወስድ ተማጽነዋል።
ነገርግን የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ መድሃኒቱን እንዲያዛውር አለመጠየቁን አስተባብሏል።
በጋዛ የድርጅቱ አባል ሻኖን ባርክሌይ በሰጡት መግለጫ በጋዛ የሚገኙት የድርጅቱ ሰራኞች በማከማቻው ውስጥ የነበረውን አብዛኛውን ወደ አዲስ ቦታ ማዘዋወር ችለዋል ብለዋል።
የአለም ጤና ድርጅት የምስራቅ ሜዲትራኒያን ዳሬክተር አህመድ አልማንድሃሪ በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በተለይም በካን ዮኒስ የምታደርገው ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል።
የድርጅቱ ባለስልጣናት በጋዛ የንጹህ መጠጥ ውሃ አለመኖሩ ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ተናግረዋል።
በኳታር አደራዳሪነት የተደረሰው ተኩስ አቀም መፈረሱን ተከትሎ ሀማስን ለማጥፋት እቅድ የያዘችው እስራኤል ጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።
ተኩስ አቁም ከተጣሰ በኋላ 800 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።