የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ ግማሽ የሚሆነው የኪቭ ግዛት አሁንም ኤሌክትሪክ አልባ ነው ተባለ
ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ያሏት ኪቭ በጭለማ እንደተዋጠች እየተገለጸ ነው
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጋ የኪቭ ግዛት ህዝብ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል
የሩሲያ ኃይሎች የሚሳይል ጥቃትን ተከትሎ ግማሽ የሚሆነው የኪቭ ግዛት አሁንም ኤሌክትሪክ አልባ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ያሏት ኪቭ በጭለማ የተዋጠችው የሚሳዔል ጥቃቱ ወሳኝ የሆኑትን የኃይል መሰረተ ልማቶችን ላይ ኢላማ ያደረገ ስለነበር ነው ተብሏል፡፡
የዩክሬን ትልቁ የግል ኢነርጂ አቅራቢ ዲቲኢኬ በሩሲያ ሚሳዔሎች 17 ጊዜያት ኢላማ ከተደረጉት ይጠቀሳል፡
በዚህም "በሚቀጥሉት ቀናት ከግዛቱ ግማሽ ያህሉ የኤሌክትሪክ ሃይል አልባ ይሆናሉ" ሲሉ የግዘቱ ርዕሰ መስተዳድር ኦሌኪይ ኩሌባ በቴሌግራም ባስተላለፉት መልእክት አስታውቋል፡፡
የዩክሬን ውስጥ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ስርዓት ኦፕሬተር (ኡክሬነርጎ )ኃላፊ ቮልዲሚር ኩድሪትስኪ በበኩላቸው የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች ሲሆን ሩሲያ ሆን ብላ ጥቃቱን እንደጀመረች ተናግረዋል ።
"በስርዓቱ ውስጥ መደበኛውን ኃይል እንደገና ለማመንጨት ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ቀናት ያስፈልጋሉ "ም ብለዋል ኩድሪትስኪ ለዩክሬን ቴሌቪዥን በሰጡት መረጃ፡፡
ከኤሌክትሪክ በተጨማሪ በግዛቱ ነዋሪዎች የውሃ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉም የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም በዩክሬን እና በሩሲያ ኃይሎች መካከል በጣም ኃይለኛ ውጊያ የተካሄደባቸውን በደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ጨምሮ በሌሎች ግዛቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል፡፡
በኦዴሳ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የውሃ ፓምፖች እና የተጠባባቂ መስመሮች የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት እና የውሃ አቅርቦት መቋረጡን በግዛቱ የሚገኝ የውሃ ኩባንያ በቴሌግራም አስታውቋል ።
በዩክሬን ቁጥጥር ስር በሚገኘው የዶኔትስክ ግዛት ውስጥ በምትገኝ ክራማቶርስክ ከተማ 370 የሚሆኑ የመኖሪያ ህንጻዎች በኤሌክትሪክ መቆራረጥ የኃይል አገልግሎት እንደሌላቸውም የከተማው ከንቲባ ተናግረዋል።
ኪቭ አንደ አንድ ከተማ በጦርነቱ ኩፉኛ ተጎድታለች ባይባልም በግዘቱ ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሲቪሎችን የመጉዳት አላማ እንደሌላት የምትናገረው ሞስኮ ዩክሬን ለሩሲያ ፍላጎት እስካልተገዛች ድረስ ጦርነቱን የፈጠረው ስቃያቸው አያበቃም ስትል እንደዛተች ነው፡፡