በዩክሬን ጦርነት የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ውለዋል መባሉ ቴህራን ውድቅ አድርጋለች
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዩክሬን የሚኖሩ የኢራን ዜጎች ለደህንነታቸው ሲሉ ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቆንስላ ዲፓርትመንት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ፤በዩክሬን ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የጸጥታ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የኢራን ዜጎች ወደዚያ ሀገር ከመጓዝ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
ዲፓርትመንቱ የኢራን ዜጎች እንዲረጋጉ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በኪቭ የሚገኘውን የኢራን ኤምባሲ ማነጋገር እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡
ዬክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ፤ሩሲያ የኢራንን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ጥቃት እያደረሰችብን ነው ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሩሲያ የጦር መሳሪያ አቅረባለች በሚል ኢራን ላይተጨማሪ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
የዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭና ሌሎች ዩክሬን ከተሞች ላይ በተሰነዘርው ጥቃትና በደረሰው ፍንዳታ የኢራን ሻሄድ 136 ድሮች ጥቅም ላይ እንደዋሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም ሩሲያ የኢራን ድሮኖችን እየተጠቀመች ነው የምትለው ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት በቴህራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጥል በመወትወት ላይ ናት።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲምትሪ ኩሌባ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት "የአውሮፓ ህብረት ለሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በማቅረብ በኢራን ላይ ማዕቀብ ሊጥል ይገባል” ብለዋል።
በዚህም መሰረት በርካታ የህብረቱ ሚኒስትሮች ኢራን በጦርነቱ ውስጥ ያላትን “ግልጽ” ተሳትፎ በመጥቀስ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
በዛሬው እለት የአውሮፓ ህብረት መሪዎች እያካሄዱት ባለው ስብሰባ በቴህራን ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከስምመነት ሊደርሱ እንደሚችሉ ሮይተርስ ከህብረቱ የውስጥ ሰዎች ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክት ዘግቧል።
በተጨማሪም አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ የኢራን አጥፍቶ ጠፊ አውሮፕላኖች በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ ውለዋል መባሉን ተከትሎ የጸጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ጠርተዋል።
ሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች መጠቀሟን እንዳይመረምር አስጠንቅቃለች፡፡
ኢራን በበኩሏ ለዩክሬን ጦርነት የምትጠቀመው ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለሩሲያ አስረክባለች የሚለውን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች፡፡