ተመድ ዩክሬን “ቆሻሻ/ደርቲ ቦምብ ልትጠቀም ነው” በሚለው የሩሲያ ክስ ዙሪያ “ገለልተኛ ምርመራ” ሊያካሂድ ነው
ፑቲን ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የዩክሬን የኒውክሌር ቦታዎችን "በተቻለ ፍጥነት" እንዲፈትሽ ጠይቀው ነበር
ዩክሬን፤ ሩሲያ "ሀሰተኛ ባንዲራ" በመጠቀም እራሷ ጥቃት ልትፈጽምብኝ ነው ስትል የሞስኮን ክስ ውድቅ አድርጋለች
የተባበሩት መንግስታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡድን “ዩክሬን ቆሻሻ/ደርቲ ቦምብ ልትጠቀም ነው” በሚለው የሩሲያ ክስ ዙሪያ “ገለልተኛ ምርመራ” እንደሚያካሂድ ገለጸ።
ሩሲያ ከሰሞኑ “ዩክሬን ቆሻሻውን ቦምብ (ደርቲ ቦምብ) ለመጠቀም አቅዳለች” ስትል ስጋቷን እየገለጸች ቢሆንም ኪቭ በተቃራኒው የሞስኮ ክስ መሰረተ ቢስ ነው ይልቁንስ"ሀሰተኛ ባንዲራ" በመጠቀም እራሷ ሩሲያ በምስራቅ እና በደቡብ ዩክሬን ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች ስትል ተደምጣለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሃላፊ ራፋኤል ግሮሲ “የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች በእነዚህ ቦታዎች ገለልተኛ ምርመራ ያካሂዳሉ” ብለዋል።
"በመከላከያ ስር ያሉ የኒውክሌር ዕቃዎችን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመቀየር፣ ማንኛቸውም ያልተፈቀዱ የኒውክሌር ቁስ ምርትን ወይም ማቀነባበሪያን በሁለቱ ቦታዎች ላይ ለመለየት እና ያልተገለጸ የኒውክሌር እቃዎች እና እንቅስቃሴዎች አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ" እንደሚሰሩ መናገራቸው ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
ኤጀንሲው "ከአንድ ወር በፊት ከሁለቱ ቦታዎች አንዱን መርምሯል እና ምንም ያልተገለጸ የኒውክሌር እንቅስቃሴ ወይም ቁሳቁስ አልተገኘም" ሲሉም አስታውሷል ሃላፊው፡፡
ቆሸሻ/ደርቲ ቦምብ በሬዲዮአክቲቭ፣ ባዮሎጂካል ወይም ኬሚካላዊ ቁሶች በፍንዳታ ውስጥ የሚሰራጭ ቦምብ ነው።
ቀደም ሲል ሐሙስ እለት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የዩክሬን የኒውክሌር ቦታዎችን "በተቻለ ፍጥነት" እንዲፈትሽ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡
ቢዚህም ምርመራው “በቀናት እና በፍጥነት” እንደሚካሄድ የኤጀንሲው ሃላፊ ግሮሲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ቫሲሊ ኔቤንዚያ "እኛ ለዋና ሃለፊው ግሮሲ ... ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ምክንያቱም እነዚህ የተመረቱት ቁሳቁሶች እንዚህ ብቻ አይደሉም ስንል ነግረናቸዋል" ብለዋል፡፡
"ግምታችን የተሳሳተ ቢሆን እኛም ደስ ይለናል"ም ነው ያሉት ኔቤንዚያ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ በመግለጽ።