በዩክሬን ጦርነት አስካሁን 400 የሚጠጉ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ዩክሬን ገለጸች
ኢራን የሚተኮሱ ሚሳይሎችንና ተጨማሪ ድሮኖችን ለሩሲያ ለመስጠት መስማማቷን መረጃዎች እየወጡ ነው
ቴህራን ለሞስኮ የምታደርገው የሰው አልባ አውሮፕላኖች ድጋፍ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተወገዘ ነው
በዩክሬን ጦርነት አስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችጥቅም ላይ ውለዋል ስትል ዩክሬን ገለጸች፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ኪቭ ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ፍንዳታዎች መከሰታቸው አንስተው በሀገሪቱን ሲቪል ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ወደ 400 የሚጠጉ ኢራን-ሰራሽ ሻሄድ-136 ካሚካዜ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሩሰያ በኩል ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።
ቀደም ብሎ በጥቅምት 17 ሩሲያ በ43 ሰው አልባ አውሮፕላኖች በዩክሬን ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሟ እንዲሁም በተመሳሳይ ቀን የሞስኮ ጦር ኪቭን ለማጥቃት 28 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተጠቅሞ አምስት ሰዎችን መግደሉ ኪቭ ኢንዲፔንደንት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በቴህራን እና በሞስኮ መካከል ያለው ግንኙነት የዩክሬኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያባብስ ነው በሚል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንዳ ከፍተኛ ውግዘት ቢገጥመውም፤ የሀገራቱ ትብብር እየጠነከረ መጥቷል፡፡
በቅርቡ ኢራን መሬት በመሬት የሚተኮሱ ሚሳይሎችን እና ተጨማሪ ድሮኖችን ለሩሲያ ለመስጠት መስማማቷን ሮይተርስ ሁለት የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣናትን እና ሁለት ድፕሎማቶችን ጠቅሶ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ስምምነቱ የተደረሰው የኢራን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሞሀመድ ሞክቤር እና ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት መሳሪያው በሚቀርብበት ጉዳይ ለመወያየት በሞስኮ ጉብኝት ባደረጉበት በፈረንጆቹ ጥቅምት ስድስት ነው፡፡
ኢራን ለሩሲያ ልትሰጥ ካሰበቸው ውስጥ ሻሃድ-136 ከአየር ወደ አየር የሚተኩስ ድሮን አንደኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ የኢራን እርምጃ ታዲያ አሜሪካን እና ሌሎች ምእራባውያን ሀገራት ሊያናድድ ይችላል ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ አቅረባለች በሚል ኢራን ላይተጨማሪ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችሉ በቅርቡ አስጠንቅቀዋል።
ዬክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ፤ሩሲያ የኢራንን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ጥቃት እያደረሰችብን ነው ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ጥቃቱ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች ላይ ያነጣጠረ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዩክሬን የኢነርጂ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረገ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የአሁን ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን ሚሳዔሎች ድብደባ የጦርነቱ መጀመሪያ አከባቢ ሞስኮ ኪቭን ለመቆጣጠር ታደርገው የነበረ መጠነ ሰፊ ጥቃት አይነት ነው ተብሏል።