ባለፉት 6 አመታት ወደ አምባገነንነት የሚያመሩ ሀገራት ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል
በ2022 የዓለም ዲሞክራሲ እያሽቆለቆለ መሆኑንም የዓለም አቀፉ የዲሞክራሲና ምርጫ አጋዥ ፋውንዴሽን ገልጿል
አሜሪካ፣ ፖላንድ እና ሃንጋሪ ዲሞክራሲ የቀነሰባቸው ሀገራት ሆነዋል
በፈረንጆቹ 2022 ከአለማችን የዴሞክራሲ ስርአት ግማሹ የመንኮታኮት አደጋ ገጥሞታል ተባለ።
መቀመጫውን በስቶክሆልም ያደረገው ዓለም አቀፍ የዲሞክራሲና ምርጫ አጋዥ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም በዓመታዊ ሪፖርቱ የዜጎች ነጻነት እና የህግ የበላይነት መጓደል በዓለም ላይ ያሉት የዲሞክራሲ ተቋማት በግማሽ እንዲቀንሱ አድርጓል ብሏል።
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ገደብ መጣልና በምርጫ ህጋዊነት ላይ እምነት ማጣት የመሳሰሉ ጉዳዮች ለዲሞክራሲ መሳሳት ማሳያ ሆነዋል።
ፋውንዴሽኑ ዲሞክራሲን የሚሸረሽሩ ሌሎች ምክንያቶችንም ዘርዝሯል። ከእነዚህም መካከል የተንሰራፋው የዋጋ ግሽበት፣ የዓለም የምጣኔ-ሀብት ውድቀት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እና የዩክሬን ቀውስ ውጤቶች ተጠቅሰዋል።
በ2022 የዲሞክራሲ ሁኔታ ላይ በተደረገው ጥናት ፋውንዴሽኑ ከ1975 ጀምሮ የተሰበሰበ መረጃ ላይ ተመርኮዝ ከዓለም የኑሮ ውድነት ጀምሮ እስከ የኒውክሌር ግጭት አደጋዎች ድረስ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ተመልክቷል።
ተቋሙ እንደ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ፣ የግል ደህንነት እና ጸጥታ የመሳሰሉ እርምጃዎችን ጨምሮ “የራሱን” የአለም አቀፍ የዲሞክራሲ አመልካቾችን አቅርቧል።
ፋውንዴሽኑ በተለይ ዲሞክራሲ የቀነሰባቸውን ሀገራትን የለየ ሲሆን፤ አሜሪካ፣ ፖላንድ እና ሃንጋሪን ከፊት አስቀምጧል።
በተለይ በአውሮፓ ውስጥ ከሚገኙት ሀገራት ግማሽ ያህሉ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ተመሳሳይ አይነት የዲሞክራሲ መሸርሸር እንዳጋጠማቸው ተመልክቷል። ሪፖርቱ ለዚህ ውድቀት የዩክሬን ቀውስ ተጠያቂ ነው ያለ ሲሆን፤ ለውጡን ለመጋፈጥ ዲሞክራሲያዊ እሴቶችን እና ተቋማትን በመሰረታዊነት ማቆየትን መክሯልም።
ዓለም አቀፍ ደረጃን በተመለከተ ሪፖርቱ እንዳመለከተው ባለፉት ስድስት አመታት ከተመዘገቡ ልኬቶች አንጻር ወደ አምባገነንነት እያመሩ ያሉ ሀገራት ቁጥር ከእጥፍ በላይ ሆኗል።
አፍሪካ ዛሬም አለመረጋጋት እያጋጠማት ቢሆንም ሪፖርቱ አዎንታዊ እድገትን ተመልክቷል። እንደ ጋምቢያ፣ ኒጀር እና ዛምቢያ ያሉ ሀገራት በዲሞክራሲ ጥራት መሻሻል አሳይተዋል ተብሏል።