የፓርላማ አባላትን ያሰሩት የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት “አምባገነን አልሆንም” አሉ
የፕሬዝዳንት ካይስ ሰይድ የሶሞኑ እርምጃዎች በቱኒዝያ ከባድ የፖለቲካ ቀውስ እንዳያስከትል ተሰግቷል
ሰይድ ወደ አምባገነንነት መቀየራቸው አይቀርም የሚልም የበርካታ የህግ ልሂቃን ስጋት እየሆነ ይገኛል
የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ሰይድ ካይስ ሁለት የሀገሪቱ ፓርላማ አባላት ያለመከሰስ መብትን በማንሳት በህግ ቁጥጥር ሰር እንዲውሉ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ፕሬዜዳንቱ ከሰሞኑ እየወሰዷቸው ያለውን እርጃ ተከትሎ “መንፈንቅለ መንግስት” እንደፈፀሙ ተደርጎ እየቀረበ ላለው ወቀሳ በሰጡት ምላሽም “አምባገነን አልሆንም” ሲሉ ተሰምተዋል።
ፕሬዚዳንት ሰይድ ካይስ ካሳለፍነው እሁድ ወዲህ እየወሰዷቸው ያሉት እርምጃዎች በርካቶችን እያነጋገሩ ሲሆን፤ በቱኒዝያ ከባድ የፖለቲካ ቀውስ እንዳያስከትል ተሰግቷል።
ፐሬዚዳንቱ ባለፉት ቀናት ብቻ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኃላፊነት ከማንሳታቸው በዘለለ የሀገሪቱ ፓርላማን ለሚቀጥሉት 30 ቀናት አግደዋል፤ እንዲሁም የካቢኔ ስልጣን ሙሉ በሙሉ ለብቻቸው ጠቅልለው ይዘዋል።
ፕሬዚዳንት ሰይድ አሁንም ቢሆን ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒሰትር እንዲሁም የሀገሪቱን ችግር ይፈታል ያሉትን ፍኖተ ካርታ ለመንደፍ ማቀዳቸው እየተሰማ ነው።
ይሁን እንጂ እየወሰድዋቸው ባሉት እርምጃዎች ትችት በማስተናገድ ላይ ናቸው፤ ፐሬዚዳንት ሰይድ ወደ አምባገነንነት መቀየራቸው አይቀርም የሚልም የበርካታ የህግ ልሂቃን ስጋት ሆኗል።
ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው በእሳቸው ዙሪያ እየተሰነዘረ ያለውን ትችት ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።
“በህገ-መንግስቱ የታፉትን በደምብ አውቀዋቸዋለሁ፤ አከብራቸዋለሁ፤ ሌሎችን አስተምሬያቸዋለሁ፤ እናም ከዚህ ሁሉ በኋላ የተወሰኑ አካላት እንደሚሉት ወደ አምባገነንነት አልለወጥም ” ሲሉም ተናግረዋል።
የዓረብ ጸደይ አብዮት መነሻ የሆነችው ቱኒዚያ የተሳካ የዴሞክራሲ አብዮት የተካሄደባት በሚል ስትነሳ የቆየች ሲሆን፤ አሁን የገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደከፋ ቀውስ ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ስጋቶች በመነሳት ላይ ይገኛሉ።