ሃማስ ግብጽ እና ኳታር ያቀረቡትን የጋዛ ተኩስ አቁም እቅድ መቀበሉንአስታወቀ
እስራኤል በበኩሏ የተኩስ አቁም እቅዱ ከሀገሪቱ መሰረታዊ ፍላጎቶች የራቀ ቢሆንም ድርድሩ እንደሚቀጥል ገልጻለች
የእስራኤል የጦር ካቢኔም የራፋህ ዘመቻው እንዲቀጥል ወስኗል
የፍልስጤሙ ሃማስ የሰባት ወራቱን የጋዛ ጦርነት ለማቆምና ታጋቾችን ለመልቀቅ ተስማምቷል።
ቡድኑ በግብጽ እና ኳታር አደራዳሪነት ለቀረበውና በሶስት ምዕራፍ ይተገበራል ለተባለው የተኩስ አቁም እቅድ ይሁንታውን መቸሩን ትናንት ማምሻውን አስታውቋል።
የሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህም ለኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ለግብጽ የደህንነት ሹም ቡድኑ በሀገራቱ አደራዳሪዎች የቀረበውን የተኩስ አቁም እቅድ እንደተቀበለው ነግረዋቸዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
እያንዳንዳቸው ለስድስት ሳምንታት ይዘልቃሉ የተባሉት ሶስት ምዕራፎች የእስራኤል ታጋቾች እና ፍልስጤማውያን እስረኞች የሚለቀቁበትን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ የሚወጣበትን እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ማካተቱ ተገልጿል።
የሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን መቀበል ዜና እንደተሰማ ፍልስጤማውያን በአደባባይ ደስታቸውን ሲገልጹ የታዩ ቢሆንም ከእስራኤል በኩል የተሰማው ምላሽ ግን ፈገግታቸውን ወዲያውኑ አክስሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አዲሱ የጋዛ ተኩስ አቁም እቅድ ከእስራኤል መሰረታዊ ፍላጎቶች የራቀ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ “እስራኤል በምትቀበለው መልኩ ስምምነት ለመድረስ ልኡካችን ልከን ድርድሩ ይቀጥላል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በሃማስ ላይ ወታደራዊ ጫና ለመፍጠርም በራፋህ የምድር ውጊያ ለመጀመር እየተደረገ ያለው ዝግጅት እንዲቀጥል የእስራኤል ጦር ካቢኔ ውሳኔ ማሳለፉንም አብራርተዋል።
እስራኤል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ወደተጠለሉባት ራፋህ ወታደሮች እና ታንኮቿን ማስጠጋቷን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከግብጽና ኳታር ጋር በመሆን በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ስታደራድር የቆየችው አሜሪካ ሃማስ ተቀብየዋለው ያለውን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ እያጤንኩት ነው ብላለች፤ የቴል አቪቭን የራፋህ ዘመቻ አሁንም ድረስ እንዳልተስማማችበትም አረጋግጣለች።
ሃማስ ተኩስ ለማቆም ተስማምቻለሁ ማለቱን ተከትሎ የኔታንያሁ አስተዳደር ከውስጥም ከውጭም ጫናው በርትቶበታል።
ታጋቾች ይለቀቁ፤ ጦርነቱ የእስራኤልን አለማቀፍ ተቀባይነት ከመቀነስ ውጪ ምንም አልፈየደም የሚሉ እስራኤላውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምምነቱን እንዲቀበሉ እየጠየቁ ነው።
ቀኝ ዘመም አጣማሪ ፓርቲዎች ደግሞ የራፋህ ዘመቻው ካልቀጠለ የኔታንያሁ መንግስት መፈራረሱ አይቀርም እያሉ እየዛቱባቸው አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል ነው የተባለው።