የእስራኤል ባለስልጣናት የአልጀዚራን ቢሮ በረበሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ግጭት ቀስቃሹ የአልጀዚራ ጣቢያ በእስራኤል ተዘግቷል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል
የእስራኤል መንግስት ባለስልጣናት የአልጀዚራ ቴሌቪዥን እንደቢሮ እየተጠቀመበት ያለውን የሆቴል ክፍል በረበሩ
የእስራኤል ባለስልጣናት የአልጀዚራን ቢሮ በረበሩ።
የእስራኤል መንግስት በእየሩሳሌም የሚገኘው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ቢሮ እንዲዘጋ ከወሰነ በኋላ ባለስልጣናት ኔትወርኩ እንደቢሮ እየተጠቀመበት ያለውን የሆቴል ክፍል መበርበራቸውን የእስራኤል ባለስልጣን እና አልጀዚራ አረጋግጠዋል።
ሲቪል የለበሱ ሰዎች በምስራቅ እየሩሳሌም በሚገኘው ሆቴል ላይ የተገጠሙ ካሜራዎችን ከጥቅም ውጭ ሲያደርጉ የሚያሳይ ቪዲዮ ኦንላይን ተለቋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኔትወርኩ የእስራኤልን ደህንነት አደጋው ውስጥ ስለጣለ የጋዛ ጦርነት እስከቀጠለ ድረስ ተዘግቶ ይቆያል ብለዋል።
የእስራኤልን ውሳኔ "የወጀል ድርጊት" ሲል የገለጸው አልጀዚራ፣ ኔትወርኩ የእስራኤልን ደህንነት አደጋ ውስጥ ጥሏል የሚለውን ክስም ጋዜጠኞችን ለአደጋ የሚያጋልጥ "አደገኛ እና የማይረባ ውሸት ነው" ሲል አጣጥሎታል።
አልጀዚራ ሁሉንም ህጋዊ አማራጮች የመጠቀም መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ገልጿል። ኔትወርኩ በዘገባዎቹ የእስራኤል ጦር በጋዛ እያካሄደ ያለውን ዘመቻ ሲተች ቆይቷል።
የእስራኤል ካቢኔ በሙሉ ድምጽ ከወሰነ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ግጭት ቀስቃሹ የአልጀዚራ ጣቢያ በእስራኤል ተዘግቷል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
መንግስት ባወጣው መግለጫ የእስራኤል የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ውሳኔው ወዲያውኑ ተፈጻሚ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፤ ነገርግን የአልደዚራን መዘጋት የሚደግፉ እንድ የፓርላማ አባል አልጀዚራ ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስደው ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
በኔትወርኩ ላይ የተላለፈው ውሳኔ በእስራኤል ውስጥ ያለውን የአልጀዚራ ቢሮ መዝጋትን፣ የስርጭት መሳሪያዎች መውረስን፣ ጣቢያውን ከሳተላይት ማውረድን እና ድረ ገጹን ማገድን ያካትታል።
የእስራኤል መንግሰት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የእስራኤል ሳተላይት እና የኬብል ቴሌቪዥን ፕሮቫይደርስ የአልጀዚራን ስርጭት አግደዋል።
የኳታር መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ መግለጫ አልሰጠም።
ኔትወርኩ፣ "አልጀዚራን ለማፈን የእስራኤል መንግስት ተከታታይ ስልታዊ ጥቃቶች" እያደረሰበት እንደሆነ ባለፈው ወር ቅሬት አቅርቦ ነበር። እስራኤል በጋዛ ጦርነት የተገደሉትን ሳመር አቡ ደቃን እና ሀምዛ አልዳህዶህን ጨምሮ በርካታ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ሆነ ብላ ኢላማ አድርጋ አጥቅታለች ብሏል አልጀዚራ። ነገርግን እስራኤል ጋዜጠኞችን አላጠቃሁም ስትል አስተባብላለች።
ኳታር አልጀዚራን ያቋቋመችው በ1996 ሲሆን በአለምአቀፍ ደረጃ ገጽታዋን ከፍ ለማድረግ ትጠቀምበታለች። "አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የሰብአዊ መብት የሚጥሰውን እና መረጃ የማግኘት መሰረታዊ መብት የሚጥሰውን ይህን የወንጀል ድርጊት በጽኑ ያወግዛል" ብሏል ኔትወርኩ ባወጣው መግለጫ።
የተመድ የሰብአዊ መብት ቢሮም የመዝጋት ውሳኔውን ተችቷል።
ካቢኔው ያሳለፈው ህግ ኔታንያሁ እና የጸጥታ ኃይላቸው የአልጀዚራን ቢሮ ለ45 ቀናት እንዲዘጉ እና እንደአስፈላጊነቱ ለማራዘም እንዲችሉ ይፈቅድላቸዋል።
በርካታ የሀማስ ፖለቲከኞች መቀመጫ የሆነችው ኳታር፣ እስራኤል እና ሀማስን እያደራደረች ትገኛለች።