ከሃማስ ጋር ተኩስ ለማቋም ብንስማማም በራፋህ የምድር ውጊያ መጀመራችን አይቀሬ ነው - ኔታንያሁ
ሃማስ እስራኤል ላቀረበችው የ40 ቀናት ተኩስ አቁም ምክረሃሳብ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ ነው ኔታንያሁ ይህን ያሉት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአጣማሪ ፓርቲዎች ራፋህን ከማጥቃት የሚያስቆም ስምምነት እንዳይደረስ ግፊት እየተደረገባቸው ነው ተብሏል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በደቡባዊ ጋዛዋ ራፋህ የምድር ውጊያ መካሄዱ አይቀሬ መሆኑን ተናገሩ።
እስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቅ ለሃማስ ያቀረበችው የ40 ቀናት የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ምላሽ በሚጠበቅበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት የድርድሩን ሂደት ያውከዋል ተብሏል።
ከሃማስ ጋር “ስምምነት ተደረሰም አልተደረሰም ወደ ራፋህ መግባታችን አይቀርም፤ በከተማዋ የመሸጉ ታጣቂዎችን ካልደመሰስን ድሉ ሙሉ አይሆንም” ማለታቸውንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በመካከለኛ ምስራቅ በስድስት ወራት ውስጥ ሰባተኛ ጉብኝታቸውን እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ እስራኤል ገብተዋል።
ሚኒስትሩ እስራኤልና ሃማስ ሊፈራረሙት የተቃረቡትን የተኩስ አቁምና የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ ስምምነት የሚያደናቅፍ ምንም አይነት ጉዳይ መኖር እንደሌለበት ነው የተናገሩት።
እስራኤል በራፋህ ለመጀመር ያሰበችውን የምድር ውጊያ በተመለከተ ግልጽ እቅዷን ታቅርብልኝ ስትል የቆየችው አሜሪካ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን የተጠለሉበት ከተማ ላይ ጦርነት መክፈት አደገኛ መሆኑን ስታሳስብ ቆይታለች።
የኔታንያሁ አስተዳደር ንጹሃንን ከከተማዋ ለማስወጣት ማቀዱን ቢገልጽም እስካሁን ዝርዝር እቅዱን ይፋ አላደረገም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአጣማሪ ፓርቲዎች (የጥምር መንግስት ከመሰረቱት) የካቢኔ አባላት እስራኤል በራፋህ ዘመቻ እንዳትጀምር የሚያግድ ስምምነት እንዳትፈራረም ጫና እየተደረገባቸው ነው ተብሏል።
የኔታንያሁ ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋዛውን ጦርነት በተመለከተ የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ከብሄራዊ ጥቅማቸው ይልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ትኩረት እንደተሰጣቸው ይገልፃሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከሀገራዊ ፍላጎት ይልቅ የጥምር መንግስታቸው መፍረስ ያሳስባቸዋል በሚል የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ግን አይቀበሉትም።
የእስራኤል የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ነው ያሉትን ሃማስ ለመደምሰስ ራፋህ ላይ የምድር ውጊያ መጀመራችን አይቀርም ሲሉም አስታውቀዋል።
ሃማስ በካይሮ ለቀረበለት የእስራኤል የ40 ቀናት ተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብም ሆነ ለኔታንያሁ አስተያየት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።