ሀማስ 33 የእስራኤል ታጋቾችን ለመልቀቅ መስማማቱ ተሰማ
የፍልስጤሙ ቡድን ከትናንት ጀምሮ በካይሮ እየተካሄደ ያለው ድርድር ስኬታማ እንዳይሆን ኔታንያሁ "እንቅፋት" ሆነዋል ብሏል
እስራኤል በበኩሏ የታጋቾች አለቃቀቅን በተመለከተ ከሃማስ የተለየ አዎንታዊ ምላሽ ካልተሰማ ተደራዳሪዎቿን ወደ ካይሮ እንደማትልክ ገልፃለች
የሰባት ወራቱን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም ትናንት በግብፅ የተጀመረው ድርድር ዛሬም ቀጥሎ ይውላል።
እስራኤል በጋዛ ለ40 ቀናት ተኩስ ለማቆምና ሁሉንም ታጋቾች ለማስለቀቅ የሚያስችል የተኩስ አቁም እቅዷን አቅርባለች።
በዚህ እቅድ ላይ ከመከረ በኋላ ትናንት ወደ ካይሮ የተመለሰው የሃማስ የተደራዳሪዎች ልኡክም ከግብፅ፣ ኳታርና አሜሪካ ተወካዮች ጋር እየመከረ ነው።
ቡድኑ እስራኤል ከጋዛ ጦሯን ሙሉ በሙሉ እንድታስወጣ የጠየቀ ሲሆን፥ በመጀመሪያው ዙርም 33 የእስራኤል ታጋቾችን ለመልቀቅ መስማማቱን አል አረቢያነ ጠቅሶ ሽንዋ ዘግቧል።
ይህም ቀደም ሲል ካቀረበው 20 ታጋቾችን የመልቀቅ እቅድ ብልጫ ያለው ነው ተብሏል።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የቡድኑ አመራር ግን እስራኤል ተወካዩዋን ያልላከችበት የካይሮው ድርድር እምብዛም ለውጥ ያልታየበት ነው ማለታቸውን ፍራንስ24 አስነብቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በግላቸው የድርድሩ "እንቅፋት" መሆናቸውን ቀጥለዋል የሚል ክስም ቀርቧል።
እስራኤል በበኩሏ ሃማስ የሚያስቀምጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አሁንም አለማሻሻሉን አስታውቃለች።
ሁሉንም ታጋቾች የሚለቅበትን ግልፅ ማዕቀፍ ካላስቀመጠ ወደ ካይሮ ተደሬዳሪዎቿን እንደማትልክ ነው የገለፀችው።
የኔታንያሁ አስተዳደር ሃማስ የሚያቀርበውን የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ይውጡ ቅድመሁኔታ በፍፁም እንደማይቀበለው በመጥቀስ ትናንት በካይሮ በተጀመረው ድርድር ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች ታይተዋል በሚል የወጡ ሪ ፖርቶችም ውድቅ አድርጋለች።
በአንፃሩ የሃማስ ታጣቂዎች መሽገውባታል ባለቻት ራፋህ ልትጀምረው ስላሰበችው የምድር ውጊያ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር መክራለች ተብሏል።