ሃማስ የእስራኤል ወታደሮች ለተገደሉበት የሮኬት ጥቃት ሃላፊነቱን ወሰደ
የእስራኤል ጦር የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ 10 ሮኬቶችን ከራፋህ ወደ ከረም ሻሎም የእርዳታ መተላለፊያ አስወንጭፏል ብሏል
የሮኬት ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል በራፋህ የአየር ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፥ የእርዳታ መተላለፊያውን ዘግታለች
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ (አል ቃሳም ብርጌድ) ሶስት የእስራኤል ወታደሮች ለተገደሉበት የሮኬት ጥቃት ሃላፊነቱን ወስዷል።
ቡድኑ በትናንትናው እለት ከራፋህ እርዳታ ወደሚተላለፍበት የከረም ሻሎም 10 ሮኬቶችን ማስወንጨፉን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
በዚህም ሶስት ወታደሮች ህይወታቸው ማለፉንና በርካቶች መቁሰላቸውን ነው ጦሩ ያስታወቀው።
አልቃሳም ብርጌድ ባወጣው መግለጫ ሮኬቶቹን ያስወነጨፈበትን ቦታ ባይገልጽም የእስራኤል ወታደሮች ወደተጠለሉበት ስፍራ ሮኬቶች መተኮሱን ገልጿል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል በራፋህ በወሰደችው የአጻፋ እርምጃ ከሶስት በላይ ንጹሃን መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል ጦርም ሃማስ ከራፋህ ሮኬቶቹን ያስወነጨፈበትን ስፍራ መደብደቡን አረጋግጧል።
“ሃማስ ከራፋህ ወደ ከረም ሻሎም መተላለፊያ ሮኬቶች ማስወንጨፉ የሽብር ቡድኑ የሰብአዊ ድጋፍ መሸጋገሪያዎችን ኢላማ እንደሚያደርግ ያሳያል፤ የጋዛ ንጹሃንን እንደ ሰብአዊ ጋሻ መጠቀሙንም ቀጥሏል” ብሏል የእስራኤል ጦር በመግለጫው።
ከጥቃቱ በኋላ እስራኤል የጋዛ የእርዳታ መተላለፊያውን ከረም ሻሎም መዝጋቷን አስታውቃለች።
ሃማስ ፍልስጤማውያን ንጹሃንን እንደ ሰብአዊ ጋሻ እየተጠቀመ ነው በሚል ከእስራኤል የሚቀርብበትን ክስ ውድቅ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።
የትናንቱ ጥቃት የሃማስ ታጣቂዎች መሽገውበታል በሚል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን የተጠለሉባትን ራፋህ ለመውረር ለተዘጋጀችው የኔታንያሁ አስተዳደር ማሳያ ሆኖለታል ተብሏል።
እስራኤል ፍልስጤማውያን በትናንትናው እለት ብቻ 19 ንጹሃን በአየር ጥቃት ከተገደሉባት ራፋህ በፈቃዳቸው እንዲወጡ መጠየቋ ተዘግቧል።
የሃማስ የሮኬት ጥቃት በካይሮ ከቅዳሜ ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው የተኩስ አቁም ድርድር ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ቢገለጽም፥ እስራኤል ከሃማስ ጋር ስምምነት ቢደረስም በራፋህ የማካሂደው የምድር ውጊያ አይቀሬ ነው ማለቷ የሚታወስ ነው።