እስራኤል በጋዛ የእግረኛ ወታደሮች እጥረት እንዳጋጠማት ተነገረ
በመንግስት ላይ የበረታው ከፍተኛ ተቃውሞ አዳዲስ ወታደሮችን ለመመልመል ሁኔታዎችን አዳጋች አድርጓል
ከጋዛ በተጨማሪ ሀገሪቱ ከሂዝቦላ ጋር የምትገኝበት ውጥረት የጦር ኃይሉ እንዲከፋፈል አድርጓል
እስራኤል በጋዛ የእግረኛ ወታደሮች ቁጥር እጥረት እንዳጋጠማት የሀገሪቱ መከለከያ ሀይል አስታውቋል፡፡
ዘጠኝ ወሩን ሊደፍን ጥቂት ቀናት የቀረው የጋዛው ጦርነት በርካታ እስራኤላዊያን ወታደሮችን ህይወት ከመንጠቁ ባለፈ በተራዘመው ጦርነት ጦሩ መሰላቸቱ ነው የተሰማው፡፡
ባሳለፍነው ሰኞ በራፋ ዘጠኝ የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል። ከዚያ ቀደም ብሎ ሃማስ ቁጥራቸው ያልተገለጸ የእስራኤል ወታደሮች በፈንጅ ስለመግደሉ አስታውቆ ነበር፡፡
የእስራኤል ጦር ዋና አዛዥ ሄርዚ ሃለቪስ በቅርብ ቀናት በጋዛ ያጋጠመው የወታደሮች እጥረት ጦርነቱን በቀደመው አቅም ለማከናወን እክል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ግዝያት በጦሩ እና በጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መካከል ያለው መቃቃር እየተባባሰ መጥቷል፤ ከሰሞኑ ሰብአዊ ድጋፎችን ወደ ጋዛ እንዲዘልቁ ውግያ አቁሙ ሲያስተባብር የነበረው የሀገሪቱ ጦር በጠቅላይ ሚንስትሩ ነቀፌታ ቀርቦበታል፡፡
በተጨማሪም ጦሩ በጋዛ እያካሄደ በሚገኝው ጦርነት የንጹሀን ፍልስጤማዊያን ሞት መጨመር ከእስራኤላዊያን ዜጎች ጭምር ቅሬታ እንዲቀርብበት አድርጓል፡፡
ባሰለፍነው ሰኞ በእየሩሳሌም ወደ ኔታንያሁ መኖርያ ቤት ለተቃውሞ ያቀኑ ሰልፈኞች የእስራኤል ጦር በጋዛ በሀማስ ተሸንፏል የሚሉ መፈክሮችን ይዘው መታየታቸው ይታወሳል፡፡
የኔታንያሁ መንግስት መበተንን እና አዲስ ምርጫ እንዲደረግ የሚጠይቁ የተቃውሞ ድምጾች በበረከቱበት ጦሩ አዳዲስ ምልምል ወታደሮችን ለመመዝገብ የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ አለመሆኑ ው የተሰማው፡፡
ጦሩ በአሁኑ ወቅት ወታደሮች ጡረታ የሚወጡበትን እድሜ ለበታች አመራሮች በአንድ አመት ከፍተኛ አመራሮችን ደግሞ በሁለት አመት የማራዘም አማራጭን ለመጠቀም እያጤነ ይገኛል፡፡
ከ8 ወራት ላለፈ ጊዜ በጋዛ እየተዋጋ የሚገኝው የእስራኤል ጦር እረፍት እና ድጋሚ መዋቀር ቢያስፈልገውም ጦርነቱ ያለ እርፍት እንዲቀጥል በመደረጉ ወታደሮች እንዲሰላቹ እና እንዲዳከሙ በማድረጉ ተልእኮዎች በቀደመው ልክ ውጤታማ እየሆኑ አይደለም፡፡
ይህ ባለበት እስራኤል በሰሜኑ የሀገሪቱ ድንበር ከሂዝቦላ ጋር የምትገኝበት ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል፡፡ የሀገሪቱ ጦር በሊባኖስ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለማወጅ የተዘጋጀው ስትራቱጂ ተቀባይነት ስለመግኝቱ በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የለንደን ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ሰላም እና ስትራቴጂክ ምሁራንን ያነጋገረው የፍራንስ 24 ዘገባ እስራኤል በሰው ሀይል ፣ በታንክ ቁጥር እንዲሁም በአጠቃላይ ወታደራዊ አቅም አጫጭር ካልሆነ ረጂም ጦርነቶችን ለማድረግ አትችልም ብሏል፡፡
ዘገባው ሀማስ እና ሂዝቦላህን የመሳሰሉ በጉሬላ የጦርነት ስልት የሚዋጉ ታጣቂዎችን በአጭር ጊዜ ጦርነት ለማጥፋት የሚከብድ ነው ብሏል፡፡
ይህን ለማስቀረት የሚደረጉ የሚሳይል እና የአየር ላይ ጥቃቶች ደግሞ በንጹሀን ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
በጋዛ በተሰላቸ ሁኔታ የሚዋጋው ወታደር ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት ሁኔታ እስራኤል የእግረኛ ጦሯን በሂዝቦላ ላይ የምታዘምት ከሆነ የሀገሪቷን ወታደራዊ አቅም የሚከፋፍል አደገኛ ውሳኔ ነው ብለዋል ተንታኞቹ፡፡