ሃማስ የሶስት እስራኤላውያን ታጋቾች እጣ ፈንታ ዛሬ እንደሚወሰን ገለጸ
የፍልስጤሙ ቡድን ታጋቾቹን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል የለቀቀ ሲሆን፥ እስራኤል በጋዛ ድብደባዋን እንድታቆም አሳስቧል
እስራኤላውያን በጋዛ ተኩስ ቆሞ ታጋቾች እንዲለቀቁ በአደባባይ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል
ሃማስ በቁጥጥሬ ስር ናቸው ያላቸውን ሶስት እስራኤላውያን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ለቋል።
መቼ እንደተቀረጸ ያልታወቀውና 37 ሰከንድ ርዝመት ያለው ምስል “ነገ (ሰኞ) እጣፈንታቸውን እንነግራችኋለን” የሚል ርዕስ ሰፍሮበታል።
ታጋቾቹ የ26 አመቷ ናኦ አርጋማኒ፣ የ53 አመቱ ዮሲ ሻራቢ እና የ38 አመቱ ኢታይ ስሪቪስኪ ናቸው ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የፍልስጤሙ ቡድን እስራኤል በጋዛ ድብደባዋን የማታቆም ከሆነ ታጋቾችን እንደሚገድል ሲዝት እንደመቆየቱ ዛሬ የሶስቱ ታጋቾች እጣ ፈንታ ሞት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ሃማስ በጥቅምት 7ቱ ጥቃት ካገታቸው ሰዎች መካከል የተወሰኑት መጥፋታቸውን አልያም በጦርነቱ ሂደት መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት 100ኛ ቀኑን በትናንትናው እለት የተለቀቀው የታጋቾች የቪዲዮ ምስልም ምናልባትም ቀደም ብሎ የተቀረጸ ሊሆን እንደሚችል ነው የተገመተው።
የሃማስ የታጋቾችን እገድላለሁ ዛቻ የስነልቦና ጦርነቱ አካል ነው የሚሉት የእስራኤል ባለስልጣናት በዛሬው እለት “እጣ ፈንታቸው ይወሰናል” የተባሉትን ታጋቾች ለማትረፍ ስለሚወሰድ እርምጃ ያሉት ነገር የለም።
ቴል አቪቭ ከዚህ ቀደምም በጋዛ እየፈጸመች ያለው ድብደባ በታጋቾች ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ተረድታ በጥንቃቄ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን የእስራኤል ጦር ቃልአቀባይ ሪር አድሚራል ዳኔል ሃጋሪ ተናግረዋል።
ሃማስ በጥቅምት 7ቱ ያልተጠበቀ ጥቃት ካገታቸው ከ240 በላይ እስራኤላውያን ውስጥ በኳታር አደራዳሪነት በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከግማሽ በላዩ መለቀቃቸው ይታወሳል።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት 132 ታጋቾች በጋዛ እንደሚገኙና 25 ታጋቾች እንደሞቱ ገልጻለች፤ በስህተት በፈጸመችው ጥቃትም ታጋች ዜጎቿን መግደሏ ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር በጋዛ ጦርነቱን በፍጥነት ማጠናቀቅ አለመቻሉና ታጋቾችን አለማስለቀቁ ተቃውሞ ማስነሳት ከጀመረ ሰነባብቷል።
በትናንትናው እለትም የታጋች ቤተሰቦችና ወዳጆች በቴል አቪቭ ጦርነት ቆሞ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ሰልፍ ተካሂዷል።
ኔታንያሁ ግን ሃማስ ካልተደመሰሰ ሁሉንም ታጋቾች ማስለቀቅ አይቻልም በሚለው አቋማቸው ጸንተው ከ24 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን የቀጠፈው ጦርነት ቀጥሏል።