100ኛ ቀኑን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እስካሁን ምን ተከሰተ?
ከ25 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የጋዛ ጦርነት ተዋናዩን እያበዛ አድማሱን ማስፋት ይዟል
የጦርነት አሸናፊ የለውም ያሉ እስራኤላውያን በቴል አቪቭ ጦርነቱ እንዲቆምና ታጋቾች እንዲለቀቁ እየጠየቁ ነው
ረጅም፣ ደም አፋሳሽ እና አውዳሚው የእስራኤል ሃማስ ጦርነት ዛሬ 100ኛ ቀኑን ይዟል።
ሃማስ ጥቅምት 7 2023 ወደ ደቡባዊ እስራኤል ሳይጠበቅ ገብቶ ጥቃት ከፈጸመና በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያንንና የሌሎች ሀገራት ዜጎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ የተቀሰቀሰው ጦርነት መቋጫ አላገኘም።
እስራኤል ሃማስን ካልደመሰስኩ ጦርነቱ አይቆምም በሚል በአየርና በምድር ጋዛን ያፈራረሱ ጥቃቶችን ፈጽማለች።
2 ነጥብ 3 ሚሊየኑ የሰርጡ ነዋሪዎችን ቢያንስ ለአንድ ጊዜ እንዲፈናቀሉ፤ ከግማሽ በላዩ የጋዛ ሆስፒታል ስራ እንዲያቆምና ረሃብ እንዲስፋፋ ያደረገው ጦርነት ያደረሰውን ውድመት በቁጥሮች እንመልከት፦
ጦርነቱ የቀጠፈው ህይወት
ፍልስጤማውያን - 23 ሺህ 968
እስራኤላውያን - 1139
በዌስትባንክ የተገደሉ ፍልስጤማውያን - 347
ህይወታቸው ያለፈ ሲቪሎች
የመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞች - 148
የጋዛ ጤና ባለሙያዎች - 337
ጋዜጠኞች - 82
ወታደሮች/ታጣቂዎች
የእስራኤል ወታደሮች - 314
የሃማስ ታጣቂዎች - ከ8 ሺህ በላይ
በጋዛ ውጊያ ላይ የተገደሉ እስራኤላውያን ወታደሮች - 187
ውድመት
የተጎዱ አልያም ሙሉ በሙሉ የወደሙ የጋዛ ህንጻዎች - ከ45 እስከ 56 በመቶ
በጋዛ ስራ ያቆሙ ሆስፒታሎች - 21
በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች - ከ69 በመቶ
የተጎዱ መስጂዶች - 142
የተጎዱ ቤተክርስቲያናት - 3
የወደሙ አምቡላንሶች - 121
መፈናቀልና ሰብአዊ ቀውስ
ከጋዛ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን - 1 ነጥብ 8 ሚሊየን (85 በመቶ ህዝብ)
የተፈናቀሉ እስራኤላውያን - 249 ሺህ 263 (2 ነጥብ 6 በመቶ ህዝብ)
ለከባድ ረሃብ የተጋለጡ ፍልስጤማውያን - 576 ሺህ
ታጋቾች/እስረኞች
ጥቅምት7 በሃማስ የታገቱ - 250 ገደማ
የተለቀቁ ታጋቾች- 121
ህይወታቸው ያለፈ ታጋቾች - 33
የተለቀቁ ፍልስጤማውያን እስረኞች- 240
የተዋናይ መበራከትና ቀጠናዊ ውጥረት
በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት በእጅ አዙር ለመፋለም የሚፈልጉ ሃይሎች በሁለቱም በኩል ይታያሉ።
ለእስራኤል ድጋፏን ያሳየችው አሜሪካ፤ ሃማስን የምታግዘው ኢራን እና ሌሎች ሀገራትም 100ኛ ቀኑን የያዘው ጦርነት ከመቆም ይልቅ አድማሱን እንዲያሰፋ ያበረታቱ ይመስላል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህና የየመኑ ሃውቲ ከሃምስ ጎን በመሰለፍ ወደ እስራኤል ጥቃት ማድረስ መጀመራቸውን ተከትሎም አሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከቧን በመላክ ጥቃቶቹ መመከት ከጀመረች ሰነባብታለች።
ቴህራንም የምታስጥቃቸው ቡድኖች በኢራቅ እና ሶሪያ በአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው የዋሽንግተንን የአጻፋ እርምጃ አስከትሏል።
የየመኑ ሃውቲ በቀይ ባህር በሚጓዙና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙ አሜሪካ ከ2016 በኋላ በየመን የአየር ድብደባ እንድትፈጽም አስገድዷል።
በጋዛ የጀመረው ጦርነት ወደ ቤሩት እና ሰንአ ተሻግሯል፤ ወላፈኑ ደማስቆ እና ባግዳድንም ነካክቷል።
በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት የተደረሱ የተኩስ አቁም ስምምነቶችም ዘላቂ መሆን ሳይችሉ 100 ቀናት ተቆጥረዋል።
እስራኤልና ሃማስ ጦርነቱን እንዲያቆሙ የሚጠይቁ ሰልፎች በተለያዩ የአለም ሀገራት አየተካሄዱ ነው።
በቴል አቪቭም የጦርነት አሸናፊ የለውም ያሉ እስራኤላውያን ጦርነቱ ቆሙ ታጋቾች እንዲለቀቁ የ24 ስአት የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ላይ ናቸው።