እስራኤል ሀማስ በስዊድን በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅዷል ስትል ከሰሰች
ባለፈው ወር የዴንማርክ ባለስልጣናት በርካታ ተጠርጣሪዎችን መያዛቸውን አስታውቀው ነበር
የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለእስራኤል ኢምባሲ ደህንነት ጉዳይ ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም
እስራኤል ሀማስ በስዊድን በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅዷል ስትል ከሰሰች።
እስራኤል የፍለስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ወደ አውሮፖ በሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ በስዊድን የሚገኘውን ኢምባሲዋን ለማጥቃት አቅዷል የሚል ክስ ማቅረቧን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፈው ወር የዴንማርክ ባለስልጣናት በርካታ ተጠርጣሪዎችን መያዛቸውን አስታውቀው ነበር።
የዴንማርክ ባለስልጣናት ተጠርጣሪዎችን መያዛቸውን ካሳወቁ በኋላ የጀርመን፣ የስዊድን ባለስልጣናት እና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ የሀማስ ኔትወርክ አባል ማግኘታቸውን ገልጸው ነበር።
ከዚህ በፊት በሚሰጣቸው መግለጫዎች ጥቃቱ በእስራኤል፣ በዌስትባንክ እና በጋዛ ሰርጥ የተገደበ መሆኑን ሲገልጽ የነበረው ሀማስ በዚህ ገዳይ ወዲያኑ መልስ አለመስጠቱን ዘገባው ጠቅሷል።
የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለእስራኤል ኢምባሲ ደህንነት ጉዳይ ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም፣ ነገርግን ስዊድን በቬና ኮንቬንሽን መሰረት የውጭ ተልእኮዎችን በቁርጠኝነት ትጠብቃለች ብሏል።
የእስራኤሉ ሞሳድ ባወጣው መግለጫ በርካታ ሀገራት ተሳትፈውበታል ያለው ምርመራ የሀማስ ኔትወርክ ከቡድኑ የማዘዣ ጣቢያ ሊባኖስ ትዕዛዝ መቀበሉን እና የእስራኤልን ኢምባሲ የማጥቃት እቅድ እንደነበረው ገልጿል።
ሀማስ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ያልተጠበቀ እና ከባድ ጥቃት በእስራኤል ላይ አድርሷል።
በሀማስ ጥቃት የተቆጣችው እስራኤል እየወሰደች ባለው የአየር ድብደባ እና የእግረኛ ጦር ጥቃት 2.3 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባትን ጋዛን ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ዳርጓታል።