ሀማስ ሁለተኛውን የታጋቾች ቡድን ቅዳሜ እንደሚለቅ አስታወቀ
ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ በሆነበት በትናንት እለት ሀማስ እና እስራኤል 3 ታጋቾችን በ90 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለዋውጠዋል
ሀማስ በሚለቃቸው ታጋቾች ምትክ እስራኤል 2000 ገደማ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመልቀቅ ተስማምታለች
ሀማስ ሁለተኛውን የታጋቾች ቡድን ቅዳሜ እንደሚለቅ አስታወቀ።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ በጋዛ ከተያዙት ታጋቾች ውስጥ በሁለተኛ ዙር ቅዳሜ እንደሚለቅ በትናንትናው እለት አስታውቋል።
የመካከለኛው ምስራቅን ያመሰቃቀለውን እና ለ15 ወራት የተዘለቀውን ጦርነቱ ባስቆመው የእስራኤል-ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ሀማስ በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ከ90 በላይ ታጋቾችን እንደሚለቅ ይጠበቃል።
ሀማስ በሚለቃቸው ታጋቾች ምትክ እስራኤል 2000 ገደማ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመልቀቅ ተስማምታለች። ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ በሆነበት በትናንት እለት ሀማስ እና እስራኤል 3 ታጋቾችን በ90 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለዋውጠዋል።
ሀማስ ባወጣው መግለጫ ቀጣዮቹ የታጋዮች ቡድን በቀጣይ ቅዳሜ በእስራኤል በተያዙ ፍልስጤማውያን እስረኞች ይለወጣሉ ብሏል። የሀማስ እስረኞች የሚዲያ ቢሮ ኃላፊ ናሄድ አል-ፋክሆሪ ቀደም ብሎ ታጋቾቹ እሁድ እንደሚለቀቁ ገልጾ ነበር። ሀማስ ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነ ከ 7 ቀናት በኋላ አራት ታጋቾችን ቅዳሜ እንደሚለቅ ይጠበቃል። ሮይተርስ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለገን የእስራኤል ባለስልጣን ጠቅሶ እንደዘገበው ታጋቾቹ የሚለቀቁበት ቀነ ገደብ ቅዳሜ ነው።
በዚህ ወር ሀማስና እስራኤል 15 ወራት የቆየውን ጦርነት የሚያስቆም በሶስት ዙር የሚተገበር ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ስድስት ሳምንት በሚፈጀው የመጀመሪያ ዙር ተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ሀማስ ሁሉንም ታጋቾች በእስረኞች በመለወጥ የሚለቅ ሲሆን የእስራኤል ኃይሎች ቀስ በቀስ ጋዛን ለቀው ይወጣሉ።