በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ6500 በላይ ሆኗል
የእስራኤል ወታደሮች እና ታንኮች በሰሜናዊ ጋዛ ድንበር አቋርጠው በመግባት በሃማስ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተገለጸ።
ትናንት ምሽት ድንበር አቋርጠው የገቡት ወታደሮች በተጠኑ የሃማስ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ መመለሳቸውንም የእስራኤል ጦር ያወጣው መግለጫ ያመላክታል።
የእስራኤል ቡልዶዘሮች ለታንኮች መንገድ ሲጠርጉ የሚያሳይ ምስልም ለቋል።
ይህም እስራኤል ለምትጀምረው የምድር ውጊያ መደላድል ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ያሳያል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ዛሬ ለሊቱን በታንኮች በተፈጸመው ጥቃት የሃማስ ተዋጊዎች መሰረተልማቶች እና ጸረ ታንክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያዎች መመታታቸውን የእስራኤል ጦር ገልጿል።
ሃማስ ግን እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የምድር ውጊያውን ለመጀመር ሀገራቸው መዘጋጀቷን በትናንትናው እለት ቢገልጹም ውጊያው የሚጀመርበትን ጊዜ ግን አልጠቀሱም።
20ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ6 ሺህ 500 መሻገሩን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ከ7 ሺህ በላይ ቆስለው ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያንም ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች መናገራቸውን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎች እና የመንግስታቱ ድርጅት የእርዳታ ድርጅቶች በነዳጅ እጥረት ምክንያት አገልግሎታቸውን እያቋረጡ ነው ተብሏል።
ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን የጋዛ ሰርጥ ነዋሪ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚጠጋው ህዝብ በጦርነቱ ምክንያት ከቀየው ተፈናቅሏል።
በእስራኤል ውሃ፣ ምግብ እና መብራት ቢከለከሉም “የትም ብንሄድ ከጥቃት አናመልጥም” ያሉ ፍልስጤማውያንም የሰቀቀን ህይወት መግፋታቸውን ቀጥለዋል።