የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ለእስራኤል ሁለተኛ የጦር ግንባር ይፈጥርባት ይሆን?
ለሃማስ አጋርነቱን የገለጸው ሄዝቦላህ የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭትን ቀጠናዊ መልክ እንዲይዝ ሊያደርገው ይችላል ተብሏል
እስራኤል በርካታ ታንኮቿን ወደ ሊባኖስ ድንበር አስጠግታለች
በደቡባዊ እስራኤል የሊባኖሱ ሄዝቦላህና የእስራኤል ጦር ተፋጠዋል።
ሃማስ ባለፈው ቅዳሜ ወደ እስራኤል ያልተጠበቀ የሮኬት ጥቃት መፈጸም ሲጀምር አስቀድሞ አጋርነቱን የገለጸው ሄዝቦላህ የእስራኤልን ራዳሮች በሮኬቶች ለመምታት ሞክሯል።
በእስራኤል የአጻፋ የቦምብ ጥቃት ሶስት ወታደሮቹ መገደላቸውም የሊባኖሱን ቡድን አስቆጥቷል ነው የተባለው።
ለሃማሳ “የእኛ ሚሳኤል የናንተ ነው፤ የኛ ሮኬት የራሳችሁ ነው” ያሉት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሮች ወደ እስራኤል ሮኬቶችን በማስወንጨፍ ቁጣቸውን ገልጸዋል።
ሄዝቦላህ ማን ነው?
ሄዝቦላህ እስራኤል ጎረቤቷን ሊባኖስ በወረረችበት በፈረንጆቹ 1982 በኢራን አቢዮታዊ ዘብ አማካኝነት የተቋቋመ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ቡድን ነው።
በሺያ ሙስሊሞች ድጋፍ የሚቸረው ሄዝቦላህ በቀጠናው የእስራኤልን ተጽዕኖ ለመግታት ከሚታገሉ ቡድኖች ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው።
የቡድኑ መሪ ሃሰን ናስራላህ በ2021 እንደገለጹት ሄዝቦላህ 100 ሺህ ተዋጊዎች አሉት፤ እስራኤል ላይ የተሳካ ጥቃት መፈጸም የሚችሉ ሮኬቶች እንደታጠቀም ሲናገሩ ይደመጣል።
ኢራን ለዚህ ቡድን በየአመቱ በመቶ ሚሊየን ዶላሮች እንደምትመድብ አሜሪካ ይፋ አድርጋለች።
ከ1992 ጀምሮ በሀሰን ናስራላህ የሚመራው ሄዝቦላህ በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ ባለው ግዙፍ ሚና በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት የሚል ቅጽል የሚሰጡት አሉ።
የሄዝቦላህ የፖለቲካ ክንፍ በምርጫ በመፎካከር በርካታ ሚኒስትሮችን በመንግስት ካቢኔ ውስጥ አስገብቷል።
በአሜሪካና ሌሎች ምዕራባዊ ሀገራት እንዲሁም በሳኡዲ አረቢያ በሽብርተኝነት የሚፈረጀው ሄዝቦላህ፥ በአውሮፓ ህብረትም ወታደራዊ ክንፉ በሽብር ተፈርጇል።
ሄዝቦላህ በእስራኤል
የሄዝቦላህ ታጣቂዎች በሊባኖስ ድንበር በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች እና በተለያዩ ሀገራት በሚኖሩ እስራኤላውያን ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
እስራኤል ከ20 አመታት ከባድ ውጊያ በኋላ ከደቡባዊ ሊባኖስ በፈረንጆቹ 2000 በተናጠል ውሳኔ መውጣቷ ሄዝቦላህ እስራኤልን መሬት ያስለቀቅኩ ብቸኛው የአረብ ታጣቂ ቡድን ነኝ አስብሎታል።
ሄዝቦላህ በ2006 ከእስራኤል ጦር ጋር “የሃምሌው ጦርነት” የተሰኘ የ34 ቀናት ውጊያ አድርጓል፤ በዚህም የ1 ሺህ 100 ሊባኖሳውያን እና 165 እስራኤላውያን ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።
በዚህ ጦርነት በርካታ ሊባኖሳውያን ህይወታቸው ቢያልፍም የእስራኤልን ጠንካራ ጦር እና የመስፋፋት ፍላጎት ያስቆምንበት ነው ይላሉ ሀሰን ናስራላህ።
ሃማስ እና ሄዝቦላህ
ከአራት ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት የከፈተው የፍልስጤሙ ሃማስም ሆነ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው።
የሃማስ ጥቃት “ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ እየጣሩ ለሚገኙ የአረብ ሀገራት ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል” ያለው ሄዝቦላህ ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን የማይቋረጥ ድጋፍ እንዳለው ገልጿል።
ሃማስ ከእስራኤል መንግስት ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነኝ ማለቱን ግን የሊባኖሱ ቡድን አልወደደውም ተብሏል።
በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፉን መቀጠሉ ጦርነቱ ቀጠናዊ መልክ እንዳይዝ ስጋት ፈጥሯል።
እስራኤልም በሊባኖስ ድንበር በርካታ ታንክና መድፎችን ደቅና እየተጠባበቀች ነው።