ሃማስ ምንድን ነው? ስለታጣቂው የፍልስጤም ቡድን ያሉ እውነታዎች
በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት የሰነዘረው ሃማስ ከ2007 ጀምሮ ጋዛን በማስተዳደር ላይ ይገኛል
የሃማስ ንቅናቄ በ1987 በኢማም ሼክ አህመድ ያሲን ነው በጋዛ የተመሰረተው
ሃማስ ድፍረት በተሞላበት መልኩ ባሳለፍነው ቅዳሜ በእስራኤል ላይ ያደረሰው ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ላይ ደም አፋሳሽ የአየር ድብዳበዎች በጋዛ እንዲፈጸሙ አድርጓል።
እስራኤል እና የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ በአንድ ቀን ውስጥ ወደ 1,000 የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
- በእስራኤልና ፍሊስጤም መካከል አዲስ ስለተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን የምናውቀው…
- የፍልስጤሙ ሃማስ ቡድን እስራኤል ላይ ለምን ጥቃት ከፈተ? ማወቅ ያለብን ነጥቦች
የሃማስ ጥቃትን ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያን ኔታንያሁ ረጅም እና አስቸጋሪ ጦርነት ውስጥ እንደገባ አድርጎናል ያሉ ሲሆን፤ የእስራኤል የጦር ጄቶችም የማያባራ የአየር ድብደባ በእስራኤል እንዲያካሂዱ በር ከፍቷል።
ሃማስ ምንድን ነው?
ሃማስ በፍልስጤም እስላማዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴን የሚመራ ታጣቂ ቡድን ነው።
ሃማስ ቡድን ጋዛ ሰርጥን በማስተዳደር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ 365 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ጋዛ ሰርጥ ከ2 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን መኖሪያ ነች።
ሃማስ ጋዛና ማስተዳደር የጀመረው በፈረንጆቹ 2007 ሲሆን፤ ቡድኑ ጋዛን የተቆጣጠረው ለፕሬዝዳንት መሃሙድ አባስ ታማኝ ኃይል ከሆነው ፋታህ ጋር ውጊያ ካደረገ በኋላ ነው።
የሃማስ ንቅናቄ በፈረንጆቹ 1987 በኢማም ሼክ አህመድ ያሲን እና አጋራቸው በነበሩት አብዱል አዚዝ አል ራንቲሲ የተመሰረተ ሲሆን፤ እስራኤል በፍልስጤም ድንብር ውስጥ የምታደርገውን ወረራ በመቃወም ነው የተመሰረተው።
በእስራኤል ወረራ ለተጎዱ ፍልስጤማውያን የማህበራዊ ደህንነት ፕሮግራሞችንም ያቀርባል።
የሃማስ ቃል አቀባይካሊድ ካዶሚ በበኩሉ፤ ቡድኑ በእስራኤል ላይ የጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ባለፉት አስርት ዓመታት ፍልስጤማውያን ላይ ለተፈጸመው ግፍ ምላሽ ነው ብሏል።
“ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በጋዛ የሚፈጸመውን ግፍ እንዲያስቆም እንፈልጋለን” ያለው ቃል አቀባዩ፤ “አል ኣቀሳን ጨምሮ ቅዱሳን ስፍራዎቻችን ለዘመቻው መጀመር መነሻ ነው” ብሏል።
መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም ፍልስጤማዊ ጦርነቱን እንዲቀላቀል ጥሪ ያቀረበው ሃማስ፤ የዌስት ባንክ ታጣቂዎች፣ የአረብ ማህበረሰብ እና ሙስሊም ሀገራት ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ በቴሌግራም በለቀቀው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።
አሁን ላይ ጦርነቱ በ7 ግንባሮች ቀጥሎ የተካሄደ ነው የተባለ ሲሆን፤ 100 ሺህ የእስራኤል ወታደሮች በምድረ ላይ ሊደረግ ለሚችል ዘመቻ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው ተብሏል።
የእስራኤል መከላከከያ ኃይል ዛሬ ባወጣው መረጃ መሰረት በሃማስ ጥቃት የሞቱ እስራኤላውኝ ቁጥር 700 የደረሰ ሲሆን፤ 2 ሸህ 150 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት በሰጡት መረጃ ደግሞ በእስራኤል የአየር ድብደባ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 413 መድረሱን እና ከ2 ሺ 300 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።