ከእስራኤል ጋር የሚደረገው ድርድር መሻሻል አለማሳየቱን ሀማስ ገለጸ
ሀማስ፣ አሜሪካ እስራኤል ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ እንዲቀበል ጫና እያደረገችብኝ ነው ሲል ቅሬታውን አሰምቷል
በአሜሪካ የሚደገፉት የአረብ አደራዳሪዎች እስካሁን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም
ከእስራኤል ጋር የሚደረገው የተኩስ አቁም ድርድር መሻሻል አለማሳየቱን ሀማስ ገለጸ።
የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ኦሳማ ሀምዳን በትናንትናው እለት እንደተናገሩት ከእስራኤል ጋር እየተደረገ ያለው የጋዛ ጦርነት ተኩስ አቁም ድርድር ምንም አይነት መሻሻል አለማሳየቱን ገልጿል።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሀማስ ጦርነቱን ሊያስቆም የሚችል ማንኛውንም የስምምነት ሀሳብን በበጎ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ሀምዳን በቤሩት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግሯል።
በአሜሪካ የሚደገፉት የአረብ አደራዳሪዎች እስካሁን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም። ለተኩስ አቁም ስምምነቱ አለመሳካት እስራኤል እና ሀማስ አንደኛቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ሀማስ ማንኛውንም የተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂ ተኩስ አቁምን እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቆ መውጣትን እንዲያካትት ሲጠይቅ፣ እስራኤል በበኩሏ ጋዛን ከፈረንጆቹ 2007 ድረስ ያስተዳደራት ሀማስ እስኪደመሰስ ድረስ ጊዜያዊ ተኩስ አቁምን ብቻ ነው የምትቀበለው።
ሀማስ፣ አሜሪካ እስራኤል ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ እንዲቀበል ጫና እያደረገችብኝ ነው ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።
"ሀማስ ዘላቂ ተኩስ አቁም እና የእስራኤል ጦርን ሙሉ በሙሉ መወጣት የሚያካትት ስምምነትን ለመቀበል ዝግጁ ነው" ያሉት ሀምዳን የታጋቾች እና የእስረኞች መቀያየር እንደሚኖርም አመላክተዋል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ድንበር በመጣስ ከባድ የተባለ ጥቃት በማድረስ 1200 ሰዎችን ሲገድል 250 ሰዎችን ደግሞ አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።
እስራኤል ይህን ጥቃት ለመበቀል በጋዛ በአየር እና በእግረኛ ጦር እየወሰደች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት ከ38ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የጋዛ የጤና ባለስልጣናት የሞቱትን ንጹሃን እና ተዋጊዎች ብሎ ባይለይም፣ አብዛኞቹ ንጹሃን ሰዎችን መሆናቸውን ግን ባለስልጣናቱ ይናጠራሉ።
እስራኤል በጦርነቱ እስካሁን 300 ወታደሮቿን ማጣቷን እና በፍልስጤም በኩል የተገደሉት አብዛኞቹ ተዋጊውች ናቸው ትላለች።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 35 ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ሼጃያ በተባለችው መንደር እያካሄደ ባለው የተጠናከረ ዘመቻ ሁለት ወታሮች እንደተገደለበት በትናንትናው አስታውቋል።
የሀማስ ታጣቂ ክንፍ ተባባሪው እስላማዊ ጂሀድ ከባድ ጦርነት መካሄዱን እና በእስራኤል ጦር ጸረ-ታንክ ሚሳይል እና ሞርተር መተኮሳቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል በዚህ ውጊያ በደርዘን የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን ገድያለሁ ብላለች። የእስራኤል ጦር የተንቀሳቀሰው በንጹሀን መንደር ነው ያለው ሀማስ ተዋጊዎች ተገድለዋል የሚለውን አስተባብለዋል።