አሜሪካ ለእስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ አውዳሚ ቦምቦች መላኳ ተገለጸ
እስራኤል እና ሄዝቦላ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ተኩስ እየተለዋወጡ ሲሆን ወደ አጠቃላይ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል
አሜሪካ ከጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጸጥታ ድጋፍ ለእስራኤል አድርጋለች
አሜሪካ ለእስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ባለ2000 ፓውንድ ክብደት ያላቸው አውዳሚ ቦምቦች መላኳ ተገለጸ
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ 10000 ባለ 2000 ፓውንድ ክብደት ያላቸውን አውዳሚ ቦምቦችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሳይሎችን ጨምሮ በርካታ ተተኳሾችን ለእስራኤል መላኩን ሁለት የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
እንደባለስልጣናቱ ከሆነ ጦርነቱ ከተጀመረት ከባለፈው ጥቅምት እስከ ቅርብ ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ አሜሪካ፣ ቢያንስ 14000 ኤምኬ-84 ባለ 2000 ፓውንድ ቦምቦችን፣ 6500 ባለ 500 ፓውንድ ቦምቦችን፣3000 ከአየር ወደ መሬት የሚተኮሱ ሚሳይሎችን፣ 1000 ከመሬት በታች ያለ ምሸግ የሚያፈርሱ ቦምቦችን፣ 2600 ከአየር ላይ የሚወረወሩ ቦምቦችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን ሰጥታለች።
እኝህ ባለስልጣናት የጦር መሳሪያዎቹ ወደ እስራኤል የተላኩበትን ቀን በዝርዝር ባይጠቅሱም፣ አሜሪካ ለአጋሯ እስራኤል የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንድታቆም ብትጠየቅም አለመቀነሷን ያሳያል ተብሏል።
ባለሙያውች እንደሚገልጹት ከሆነ ግን አሜሪካ እስራኤል ለስምንት ወር በዘለቀው የጋዛ ጦርነት የተመናመነባትን የመሳሪያ ክምችት ለመሙላት በቋሚነት እየላከች ነው።
አሜሪካ የላከችው የጦር መሳሪያ ዝርዝር "አሜሪካ ወሳኝ ለሆነችው አጋራችን እስራኤል ወሳኝ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነ በግልጽ ያሳያል" ሲሉ በስትራቴጂክ እና አለምአቀፍ ግንኙነት ማዕከል የጦር መሳሪያ ባለሙያ የሆኑት ቶም ካራኮ ተናግረዋል።
ባለሙያው እንዳሉት የተዘረዘሩትን መሳሪያዎች እስራኤል ከሄዝቦላ ወይም ከሀማስ ጋር በሚኖረው ግጭት የምትጠቀምባቸው ናቸው።
እስራኤል እና ሄዝቦላ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ተኩስ እየተለዋወጡ ሲሆን ወደ አጠቃላይ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።በዚህ ጉዳይ አሜሪካ በይፋ ያለችው ነገር የለም ተብሏል።
አንደኛው ባለስልጣን እንዳሉት እነዚህ መሳሪያዎች አሜሪካ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የላከችው የትልቁ ዝርዝር አካል ናቸው። አሜሪካ ከጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጸጥታ ድጋፍ ለእስራኤል አድርጋለች።