በኢስማኤል ሃኒየህ የተመራ የሃማስ ልኡክ ግብጽ ገባ
ሃኒየህ በራፋህ ወቅታዊ ጉዳይ እና በእስረኞችና ታጋቾች ልውውጥ ዙሪያ ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሏል
እስራኤል ሃማስ ያቀረበውን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ “ቅዠት” ነው በሚል ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል
በሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ የተመራ ልኡክ በዛሬው እለት ካይሮ ገብቷል።
የቡድኑን ከፍተኛ የፖሊት ቢሮ አቫል ካሊል አልሃያ ያካተተው ልኡክ በራፋህ ወቅታዊ ሁኔታና በታጋች እና እስረኛ ልውውጥ ድርድሩ ዙሪያ ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር ይወያያል ተብሏል።
137ኛ ቀኑን የያዘውን ጦርነት የሚያስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየው ንግግር እስካሁን ተጨባጭ ውጤት አላሳየም።
እስራኤል ጦርነቱን ለማራዘም ፍላጎት አላት ስትል የወቀሰችው ዶሃም የተኩስ አቁም ድርድሩ “ተስፋ ሰጪ” አይደለም የሚል መግለጫን ማውጣቷ ይታወሳል።
እስራኤል ሁሉም ታጋቾች ካልተለቀቁ የረመዳን ጾም መጀመሪያ ላይ በራፋህ የእግረኛ ጦሯን በማስገባት ጦርነት እንደምትጀምር ማሳወቋም ድርድሩ ላይ ጥላ ማሳረፉና ካይሮንም ስጋት ውስጥ መጣሉ ተገልጿል።
የፍልስጤሙ ቡድን በሶስት ምዕራፍ የሚተገበርና ለ135 ቀናት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ሃሳብ አቅርቦ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ቅዠት” ነው ተብሎ ውድቅ መደረጉ አይዘነጋም።
በዶሃ የሚገኘው የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ እና ልኡካቸው በካይሮ የሚያደርገው ንግግርም ከ29 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ጦርነት በፍጥነት ያስቆማል ተብሎ አይጠበቅም።
በሌላ ዜና የጸጥታው ምክርቤት በዛሬው እለት በአልጀሪያ በቀረበው የጋዛ ተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
በጸጥታው ምክርቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ በጋዛ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዳይደረስ ስታደርግ የቆየችው አሜሪካም “ጊዜያዊ ተኩስ አቁም” እንጂ ጦርነቱ እንዲቆም እንደማትፈልግ ለሶስተኛ ጊዜ አቋሟን ታንጸባርቃለች ተብሏል።
ፍልስጤማውያን በሃይል ከመኖሪያቸው እንዳይፈናቀሉ የሚጠይቀው በአልጀሪያ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በራፋህ ጦርነት ለመጀመር ቀነ ገደብ ባስቀመጠችው እስራኤል እና በአጋሯ አሜሪካ ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ እንደማይጠበቅ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።