የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ ምክትል አዛዥ ማርዋን ኢሳ መገደሉን አሜሪካ አስታወቀች
የሀማስ ወታራዊ ክንፍ አል ቃሴም ብርጌድ ምክትል አዛዥ የሆነው ኢሳ በእስራኤል በዋና ተፈላጊ ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ነበር
ማርዋን ኢሳ የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ የተገደለ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ነው ተብሏል
የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ ምክትል አዛዥ ማርዋን ኢሳ መገደሉን አሜሪካ አስታወቀች።
የሀማስ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሆነው ማርዋን ኢሳ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን የኃይት ሀውሱ ባለስልጣን ጄክ ሱሊቪያን ገልጸዋል።
ማርዋን ኢሳ የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ የተገደለ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ነው ተብሏል።
ጋዛን የተቆጣጣረው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ግን ማርዋን ኢሳ ሞቷል በሚለው ሪፖርት ጉዳይ በይፋ ያለው ነገር የለም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን የጋዛው ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለስድስተኛ ጊዜ በዚህ ሳምንት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያቀናሉ። ብሊንከን በሳኡዲ አረቢያ እና በግብጽ የተኩስ ተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ታጋቾች እንዲለቀቁ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።
እስራኤል በግብጽ ድንበር የምትገኘዋን የጋዛዋን ራፋ ከተማ ለማጥቃት የያዘችውን እቅድ ብታጸድቅም፣ በኳታር እየተካሄደ ያለው ድርድር እንደቀጠለ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የእስራኤል ራፋን የማጥቃት እቅድ "ስህተት ነው" ሲሉ ለእሰራኤሉ ጠቅላይ ማኒስትር ኔታንያሁ ተናግረዋል።
ሮይተርስ የእሰራኤል የመገናኛ ብዙኻን ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ኢሳ ከሳምንት በፊት የተገደለው እስራኤል በኑሰራት የስደተኞች ካምፕ ስር በሚገኘው ቱቦ ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ነው። የሀማስ ወታራዊ ክንፍ አል ቃሴም ብርጌድ ምክትል አዛዥ የሆነው ኢሳ በእስራኤል በዋና ተፈላጊ ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ነበር።
ሀማስን በሽብርተኝነት የፈረጀው የአውሮፖ ህብረት ኢሳ ጥቅምት ወር በእሰራኤል ላይ ለተፈጸመው ጥቃት እጁ አለበት ብሏል።
ማርዋን ኢሳ በመጀመሪያው የፍልስጤም ኢንቲፋዳ በእሰራኤል ለአምስት አመታት ታስሮ ነበር። የፍለስጤም አስተዳደርም ማርዋን ኢሳን ከ1997 ጀምሮ ሁለተኛው ኢንቲፋዳ እስከሚጀምርበት 2000 ድረስ አስሮት ቆይቷል።
እስራኤል ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በርካታ የሀማስ አመራሮችን መግደሏን መግለጿ ይታወሳል።
የሀማስ የፖለቲካ መሪ ሳለህ አል አሮሪ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ደቡባዊ ጫፍ በደረሰ ፍንዳታ ተገድሏል። ይህን ጥቃት ያደረሰችው እስራኤል ነች ተብሎ ይታመናል።
የኃይት ሀውስ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ሱሊቫን ሌሎች የሀማስ መሪዎችም በሀማስ የቱቦ ወይም የመሬት ውስጥ ዋሻ ተደብቀው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
አማካሪው እሰራኤል ከፍተኛ የሀማስ መሪዎችን ለመግደል የምታደርገውን አሰሳ አሜሪካ ትደግፋለች ብለዋል። እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች በኋላ ያስገኘችውን ስኬት የጠቀሱት ሱሊቫን በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ግን እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።