ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ሀማስ ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አደረጉ
ስምምነት ተደርጎ ቀሪዎቹ ታጋቾች እንዲለቀቁ ቤተሰቦቻቸው ቢወተውቱም፣ እስራኤል ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት አላሳየችም
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ሀማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ እስራኤል ጦርነቱን አቁማ ሙሉ በመሉ እንድትወጣ ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል
ኔታንያሁ ሀማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አደረገዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ እስራኤል ጦርነቱን አቁማ ሙሉ በመሉ እንድትወጣ እና ሃማስ በጋዛ ስልጣኑን እንዲይዝ ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ ማድረጋቸውን በትናንትናው እለት አስታውቀዋል።
የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገረው እስራኤል በካን ዮኒስ የምታደርገውን ድብደባ ቀጥላለች
ባለስልጣኑ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ጥቃት የማታቆም ከሆነ ታጋቾቹ አይለቀቁም ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል።
"የታገቱብንን ለመልቀቅ፣ ሀማስ በምትኩ ጦርነቱ እንዲቆም፣ ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንድንወጣ እና ሁሉም ደፋሪዎች እና ገዳዮች እንዲለቀቁ ይፈልጋል" ሲሉ ኔታንያሁ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል።
"ሀማስ እንደነበረ እንዲተውም ይፈልጋል"
ኔታንያሁ ይህን ጥያቄ እንደማይቀበሉት ግልጽ አድርገዋል።
ባለፈው ህዳር በኳታር አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሀማስ አግቷቸው ከነበሩት 240 ሰዎች ውስጥ 100 የሚሆኑትን ሲለቅ በምትኩ እስራኤል ያሰረቻቸውን 240 ፍልስጤማውያንን መልቀቋ ይታወሳል።
ስምምነት ተደርጎ ቀሪዎቹ ታጋቾች እንዲለቀቁ፣ የታጋቾች ቤተሰቦች ቢወተውቱም፣ እስራኤል ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት አላሳየችም።
ባለፈው ሳምንት ኔታንያሁ በቴሌቪዥን በተላለፈ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቀርበው እስራኤል የሀማስ ታጣቂዎችን ሳታጠፋ እና ሁሉንም ታጋቾች ሳታስለቅቅ ጥቃቷን እንደማታቆም ተናግረዋል።
እነዚህ ግቦች አያሳኩም የሚሉ ትችቶችን ውድቅ ያደረጉት ኔታንያሁ ጥቃቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዝተው ነበር።
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ሀማስ ያልተጠበቀ የሚባል ጥቃት በእስራኤል ማድረሱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰለማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ ቀጣናዊ ውጥረትም እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።