የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም ስምምነት ቀጥሎ ትናንት 110 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተፈተዋል
የፍልስጤሙ ቡድን ሃማስ ወታደራዊ አዛዡ መሀመድ ዴይፍ መገደሉን ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋግጧል።
የእስራኤል ጦር ዴይፍን ባለፈው አመት ሀምሌ ወር ላይ በካን ዩኒስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት እንደተገደለ ብትገልጽም ሃማስ እስከ ትናንት ድረስ ማረጋገጫ አልሰጠም ነበር።
እስራኤል 1 ሺህ 200 ገደማ ሰዎች የሞቱበትን የጥቅምት 7ቱን የሃማስ ጥቃት "ያቀደው፣ ያቀነባበረና ያስፈጸመ" ነው በሚል የምትወቅሰው መሀመድ ዴይፍ ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ መሪ ሆኖ አገልግሏል።
በ1985 በካን ዩኒስ የስደተኞች ጣቢያ የተወለደው ዴይፍ ትክክለኛ ስሙ መሀመድ ዲያብ አል ማስሪ እንደነበርም ፍራንስ 24 አስታውሷል።
ዴይፍ የሃማስ ተዋጊዎች በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ለመፈጸም የተጠቀሙባቸውን የምድር ውስጥ መተላለፊያ ዋሻዎች በማስገንባትና የቃሳም ብርጌድ መተማመኛ የሆነውን "ቃሳም ሮኬት" በማሰራት ስሙ በጉልህ ይነሳል።
ከእስራኤል ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ያመለጠው መሀመድ ዴይፍ አሜሪካ በ2015 ከአለማቀፍ አሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ አስገብታው ነበር።
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤትም ባለፈው አመት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዛዣ ሲያወጣ መሀመድ ዴይፍም መካተቱ አይዘነጋም።
ሃማስ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ የዴይፍ ምክትል የነበረው ማርዋን ኢሳም መገደሉን አረጋግጧል።
አሜሪካ ባለፈው አመት መጋቢት ወር ኢሳ መገደሏን ማስታወቋ የሚታወስ ሲሆን፥ በሃማስ መግለጫ ኢሳ መቼና እንዴት እንደተገደለ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።
ሃማስ የወታደራዊ መሪዎቹን መገደል ያረጋገጠው ሶስተኛው ዙር የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ በተካሄደበት እለት ነው።
ሶስት እስራኤላውያን እና አምስት ታይላንዳውያን ታጋቾች በተለቀቁበት እለት እስራኤል 110 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
በፈረንጆቹ ጥር 19 2025 ተግባራዊ መደረግ ከጀመረው ተኩስ አቁም ወዲህ 15 ታጋቾች የተለቀቁ ሲሆን፥ እስራኤል 400 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።