እስራኤል አጥብቃ የምትፈልገው የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪ መሀመድ ዴይፍ ማን ነው?
ዴይፍን ኢላማ ባደረገው የእስራኤል ጥቃት የሟቾች ቁጥር 90 የደረሰ ሲሆን፥ ከ300 በላይ ሰዎች ቆስለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ዴይፍ ስለመገደሉ እስካሁን እርግጠኛ ባንሆንም በሁሉም የሃማስ አመራሮች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ይቀጥላሉ ብለዋል
እስራኤል በትናንትናው እለት በጋዛ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪውን መሀመድ ዴይፍ ለመግደል ሙከራ አድርጋለች።
በደቡባዊ ጋዛ ዴይፍን ኢላማ አድርጋ በፈጸመችው ጥቃትም የሟቾች ቁጥር 90 የደረሰ ሲሆን፥ ከ300 በላይ ንጹሃን መቁሰላቸውንም የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸው አጥብቃ የምትፈልገው መሀመድ ዴይፍ ስለመገደሉ “እስካሁን እርግጠኛ መሆን አልቻልንም” ብለዋል።
ኔታንያሁ ጥቃቱን ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ የሃማስ ሁሉም አመራሮችን ለመግደል የእስራኤል ጦር የሚፈጽማቸውን የተጠኑ ጥቃቶች ይቀጥላል ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው መሀመድ ዴይፍ ማን ነው?
ዴይፍ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ (አል ቃሳም ብርጌድ) በፈረንጆቹ 1990 ከመሰረቱ የሃማስ መሪዎች መካከል አንዱ ነው።
እስራኤል ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የአልቃሳም ብርጌድን ሲመራ የቆየው ዴይፍ ከሃማስ የጋዛ መሪው ያህያ ሲንዋር ጋር በመሆን የጥቅምት 7ቱን ጥቃት እንዳቀነባበረ ታምናለች።
ከሰባት በላይ የእስራኤል የግድያ ሙከራዎችን ያመለጠው ዴይፍ አንድ አይኑን ማጣቱ የሚነገር ሲሆን፥ በአደባባይ ከታየ አመታት ተቆጥረዋል።
“ዴይፍ” በአረብኛ እንግዳ የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን፥ መሀመድ ዴይፍም የእስራኤል የማያቋርጥ የግድያ ሙከራ ለማምለጥ እንደ እንግዳ በየእለቱ አቅጣጫውን ይለውጣል።
አንዳንዶች የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው በእስራኤል ጥቃት በደረሰበት ጉዳት በዊልቼር እንደሚንቀሳቀስ ሲገልጹ ይደመጣል።
በኦንላይን ላይ የሚገኙ የመሀመድ ዴይፍ ምስሎች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን፥ ከእይታ እየተሰወረ ተደጋጋሚ የእስራኤል ጥቃቶችን በማምለጡም “ስውሩ ሰው” የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለታል።
እንደ ያህያ ሲንዋር ሁሉ በደቡባዊ ጋዛዋ ካን ዩኒስ በስድተኞች ጣቢያ የተወለደው ዴይፍ በ1980ዎቹ ሃማስን እንደተቀላቀለ ይገመታል።
በ1989 በፍልስጤማውያን “መቅሰፍት” ወይም ኢንቲፋዳ ወቅት በእስራኤል ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ ብዙም ሳይቆይ የተለቀቀው መሀመድ ዴይፍ እስራኤል የሃማስን ወታደራዊ ክንፍ መሪ ከ22 አመት በፊት ስትገድል ወደ መሪነት መጥቷል።
ሃማስ በጋዛ ረጃጅምና ሰፊ የመሬት ውስጥ መተላለፊያ ዋሻዎችን እንዲገነባ ማገዙና በእስራኤላውያን ላይ ያነጣጠሩ የቦምብ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ማድረጉም ይነገርለታል።
የአልቃሳም ብርጌድ በራሱ አቅም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያመርት በማስቻሉ ረገድም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የሚነገረው።
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትርና በመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ሲጠይቁ መሀመድ ዴይፍና ያህያ ሲንዋርንም ማካተታቸው ይታወሳል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በደቡባዊ ጋዛ በፈጸመችው ጥቃት መሀመድ ዴይፍ ከተገደለ ለሃማስ ከፍተኛ ኪሳራ ለቴል አቪቭ ደግሞ ትልቅ ድል ይሆናል።
ተንታኞች ዴይፍ ከተገደለ የተጀመሩ የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድሮችን እንደሚያውክና መለሳለስ እያሳየ የነበረውን ሃማስ ወደቀደመ ጠንካራ አቋሙ ሊመልሰው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።