ታጋቾችን ለመጉዳት የሚሞክር አካል ዋጋ ይከፍላል - ኔታንያሁ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ በካን ዩኒስ ታጋቾች ሲለቀቁ የታየውን "አስደንጋጭ ክስተት" አውግዘዋል
እስራኤል 110 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትለቅ ይጠበቃል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ በካን ዩኒስ ታጋቾች ሲለቀቁ የታየውን "አስደንጋጭ ክስተት" አወገዙ።
ሃማስ ሶስት እስራኤላውያን እና አምስት ታይላንዳዊያን ታጋቾችን ከ15 ወራት እገታ በኋላ ለአለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር አስረክቦ እስራኤል ገብተዋል።
የ20 አመቷ የእስራኤል ወታደር አጋም በርገር ስትለቅ ሰላማዊ ሂደት የነበረ ሲሆን፥ ሰባቱ ታጋቾች ከካን ዩኒስ ሲለቀቁ ትርምስ ተፈጥሮ እንደነበር የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
የቀይ መስቀል ተሽከርካሪዎች በፍልስጤማውያን ተከበው ታጋቾቹን ወደ ተሽከርካሪዎቹ የማስገባቱ ሂደት ከአንድ ስአት በላይ ተጓቷል።
ሁለቱ የእስራኤል ታጋቾች (አርበል የሁድ እና ጋዲ ሞሰስ) ሲለቀቁ በበርካታ ሰዎች ተከበው ሲገፈታተሩ መታየቱ የእስራኤል ባለስልጣናትን አስቆጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በካን ዩኒስ የተፈጠረውን ክስተት "አስደንጋጭ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን እንዳይደገም አስጠንቅቀዋል።
"የታጋቾች ደህንነት መጠበቅ አለበት፤ አደራዳሪዎች ይህን መሰሉ አሰቃቂ ነገር እንዳይደገም ማረጋገጫ እንዲሰጡን እንጠይቃለን" ብለዋል።
ኔታንያሁ "ማንኛውም ታጋች ዜጋችን ለመጉዳት የደፈረ ዋጋውን ያገኛል" ሲሉም ዝተዋል።
እስራኤል በዛሬው እለት 110 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትለቅ እየተጠበቀ ነው።
ሃማስ በሶስት ዙሮች 15 ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን፥ እስራኤል ዛሬ የምትለቃቸውን ሳይጨምር 290 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
ዛሬ ከሚለቀቁት ፍልስጤማውያን ውስጥ 32ቱ የእድሜ ልክ እስራት ተላልፎባቸው የነበረ ሲሆን፥ 30ዎቹ ደግሞ ህጻናት መሆናቸውን ሃማስ ይፋ አድርጓል።