እስራኤል ገድየዋለው ያለችው የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ ምክትል አዛዥ ማርዋን ኢሳ ማን ነው?
“ጥላቢሱ” የሚል ቅጽል ስም የወጣለት ኢሳ የእስራኤልን ሶስት የግድያ ሙከራዎች አምልጧል
ማርዋን ኢሳ በጋዛ የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ወይም የአልቃሳም ብርጌድ አዛዡ መሀመድ ዴይፍ ቢሞቱ ይተካቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ቁልፍ አመራር ነበር ተብሏል
እስራኤል የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ ምክትል አዛዥ ማርዋን ኢሳን መግደሏን አስታውቃለች።
ኢሳ በማዕከላዊ ጋዛ ኑሲራት የስደተኞች ጣቢያ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደሉን አሜሪካ እና የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
የፍልስጤሙ ቡድን ሃማስ ግን እስካሁን ስለ ማርዋን ኢሳ ግድያ ማረጋገጫ አልሰጠም።
ኢሳ የጥቅምት 7ቱን ጥቃት ካቀናበሩት የሃማስ አመራሮች ውስጥ አንደኛው ነው የምትለው እስራኤል በጋዛ አጥብቃ ከምትፈልጋቸው የሃማስ አመራሮች በሶስተኛ ደረጃ አስቀምጣው ነበር።
ማርዋን ኢሳ የእስራኤልን ሶስት የግድያ ሙከራዎች (በ2006፣ 2014 እና 2021) ማምለጡ “ጥላቢሱ” የሚል ቅጽል ስም እንዲወጣለት አድርጓል።
በማዕከላዊ ጋዛ ቡረጂ በተባለ አካባቢ በፈረንጆቹ 1965 የተወለደው ኢሳ በአደባባይ የሚታይ ሰው ባለመሆኑ እንደ ያህያ ሲንዋር እና መሀመድ ዴይፍ ታዋቂ አልነበረም።
ይሁን እንጂ ባለፉት አመታት የሃማስ ውሳኔዎች ቁልፍ ድርሻ ነበረው፤ በቅርቡም ሃማስ ከእስራኤል ጋር የእስረኛ እና ታጋች ልውውጥ ሲያደርግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
በመጀመሪያ የፍልስጤማውያን አመጽ (ኢንቲፋዳ) ለአምስት አመት በእስራኤል የታሰረው ማርዋን ኢሳ፥ የፍልስጤም አስተዳደርም ከ1997 እስከ 2000 (ሁለተኛው ኢንቲፋዳ) አስሮት እንደነበር የዘናሽናል ዘገባ ያወሳል።
የ58 አመቱ ጎልማሳ የእስራኤልን የግድያ ሙከራዎች እያመለጠ ሃማስን በማደራጀቱ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
በተለይ ከእስራኤል ጋር በሚደረጉ የእስረኞች ልውውጥ ልዩ የመደራደር አቅም እንደነበረው ነው የሚነገረው።
እስራኤል ጊላድ ሻሊት የተባለ ወታደሯን ለማስለቀቅ 1 ሺህ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመፍታት ስትስማማም መደበኛ ያልሆነ ድርድሩን መርቷል።
ማርዋን ኢሳ በ2021 ከአልጀዚራ ጋር ባደረገው ቆይታ “የፍልስጤማውያን የነጻነት ትግል በእያንዳንዱ ስአት በጠላት ክትትል ውስጥ ቢሆንም ሁሌም እንዳስገረምናቸው” ነው ሲል ገልጾ ነበር።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ ምክትል አዛዥ ከሆነ ወዲህም በቡድኑ ደጋፊዎች የሚያስወድሱትን ተግባራት መፈጸሙ ነው የተገለጸው።
የአል ቃሳም ብርጌድ አዛዡ ሞሀመድ ዴይፍ ቀኝ እጅ ነው የሚባልለት ኢሳ በሃማስ ወታደራዊ ክንፍ ብቻ ሳይሆን በያህያ ሲንዋር በሚመራው የጋዛ የፖለቲካ ቢሮ ውስጥም ተሳትፎ ያደርጋል።
ሲንዋር ወይም ዴይፍ ቢያልፉ እንዲተካቸው ዝግጁ መደረጉም ሲገለጽ ቆይቷል።
እስራኤል ግን “ጥላቢሱ”ን ሰው ለአስርት አመታት በሽብርተኝነት ፈርጃ ስትፈልገው ነው የከረመችው።
አሜሪካ በ2019 እና የአውሮፓ ህብረት ደግሞ ከጥቅምት 7ቱ ጥቃት በኋላ ማርዋን ኢሳን በልዩ የአለማቀፍ ሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ ማስገባታቸው ይታወሳል።
ማርዋን ኢሳ የሁለት ወንድ ልጆች አባት መሆን ቢችልም አድገው ትግሉን ሊያስቀጥሉለት አልቻሉም።
ባራ የተባለው ልጁ በጽኑ ታሞ ከጋዛ ሰርጥ ወደ ግብጽ ገብቶ መታከም ቢኖርበትም ካይሮ ባለመፍቀዱ ህይወቱ አልፏል።
ሙሀመድ የተባለው ልጁ ደግሞ በ2023 እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት መገደሉ ተገልጿል።
“ጥላቢሱ” የእስራኤልን ገድየዋለው ዜና ውድቅ አድርጎ ዳግም ሊታይ ይችላል የሚለው የበርካታ ደጋፊዎቹ ምኞት ነው።