ሀማስ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ታጋቾች ሊለቅ ይችላል - በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር
አምሳደሩ ይህን ያሉት የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በሀማስ እና በእስራኤል መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር "ጥቂት ነገር" ብቻ ይቀራል ማለታቸውን ተከትሎ ነው
ዋይትሃውስ በበኩሉ "ውስብስቡ እና አስቸጋሪ" የሆነው ድርድር መሻሻል እያሳየ ነው ብሏል
በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ሀማስ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ታጋቾች ሊለቅ እንደሚችል በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ተናግረዋል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ከባድ የተባለ ጥቃት በሰነዘረቀት ወቅት 240 የሚሆኑ ሰዎችን አግቶ ወስዷል። በዚህ ድርጊት የተቆጣችው እስራኤል ጋዛን ወርራ ሀማስ ይገኝበታል የምትለውን ቦታ በአየር እና በእግረኛ ጦር በማጥቃት ላይ ትገኛለች።
በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ሚካኤል ሄርዞግ ሀማስ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ በርካታ ታጋቾችን ይለቃል ብለው ተስፋ እንደማያደርጉ ተናግረዋል።
አምሳደሩ ይህን ያሉት የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በሀማስ እና በእስራኤል መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር "ጥቂት ነገር" ብቻ ይቀረዋል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ሼህ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ በዋናነት "የተግባር እና የሎጂስቲክ" ጉዳዮች እንደቀሩት የገለጹ ሲሆን ኃይትሀውስ በበኩሉ "ውስብስቡ እና አስቸጋሪ" የሆነው ድርድር መሻሻል እያሳየ ነው ብሏል።
እስራኤል ጦርነቱን ለአምስት ቀናት ያህል ጋብ እንድታደርግ እና ሀማስ ደግሞ ታጋቾችን እንዲለቅ ለማድረግ ድርድር እየተደረገ ነው መባሉ ይታወሳል።
በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ አለምአቀፍ ጫና ቢደረግም፣ እስራኤል ጦርነቱን ጋብ ከማድረግ ውጭ ሀማስን ሳታጠፋ እንደማታቆም ደጋግማ አሳውቃለች።