የእስራኤል ጦር አል ሽፋ ሆስፒታልን ወረር፤ ሀማስ እጅ እንዲሰጥ ጠየቀ
የእስራኤል ጦር ወደ ጋዛ መሀል ከተማ ገብቶ አል ሽፋ ሆስፒታልን ከመክበቡ በፊት ለተከታታይ 10 ቀናት ከሀማስ ጋር ተዋግቷል
እስራኤል በትናንትናው እለት በሆስፒፓሉ ውስጥ ሀማስ የማዘዣ ጣቢያ አድርጎ ሲጠቀምበት ነበር ያለችውን 'ቤዝመንት' በፎቶ እና ቪዲዮ አሳይታለች
የእስራኤል ጦር በዛሬው እለት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ንጹሃን የተጠለሉበትን ግዙፉን አል ሽፋ ሆስፒታልን መውረሩን እና ሀማስ እጅ እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረቡን ገልጿል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በሆስፒፓሉ ውስጥ ሀማስ የማዘዣ ጣቢያ አድርጎ ሲጠቀምበት ነበር ያለችውን 'ቤዝመንት' በፎቶ እና ቪዲዮ አሳይታለች።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ በስላላ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ በተመረጡ የሆስፒታሉ ክፍሎች ላይ ኢላማውን የጠበቀ ጥቃት እንደሚከፍት አስታውቋል።
ጦሩ እንደገለጸው ንጹሃንን እንዳይጎዱ ጥንቃቄ በማድረግ ዘመቻው ይከወናል ብሏል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሌትናንት ኮሎኔል ፒተር ለርነር ለሲኤንኤን እንደተናገሩት ሀማስ ሆስፒታሉን እና ግቢውን "የዘመቻ መምሪያ" አድርጎታል።
አሜሪካም በራሷ ደህንነት ያገኘችው መረጃ የእስራኤልን ድምዳሜ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጻለች።
ሀማስ አሜሪካ ይህን ማለቷ እስራኤል ሆስፒታሉን እንድትወር ፍቃድ የሚሰጥ ነው ብሏል። ቡድኑ ለዚህ ዘመቻ እስራኤል እና የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ሲል ተናግሯል።
የኋይት ሀውስ የብሔራዊ ደህንነት ካውንስል ቃል አቀባይ "ሆስፒታል በአየር እንዲደበደብ አንደግፍም፤ በሆስፒታል ውስጥ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ፣ የታመሙ እና የሚረዳቸው ያጡ ንጹሃን ሰዎች በጦርነት ቀጣና ውስጥ ሲገቡ ማየት አንፈልግም" ብለው ነበር።
የእስራኤል ጦር ወደ ጋዛ መሀል ከተማ ገብቶ አል ሽፋ ሆስፒታልን ከመክበቡ በፊት ለተከታታይ 10 ቀናት ከሀማስ ጋር ተዋግቷል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ ድንበር በመጣስ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ የተባለ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነሰፊ ጥቃት እያካሄደች ትገኛለች።
ሀማስ እስራኤል በእግረኛ ጦር ወደ ጋዛ መግባት ስትጀምር ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ የነበረ ቢሆንም እስራኤል አልተቀበለችውም።
በጦርነቱ በጋዛ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ በመፈጠሩ ምክንያት ተመድ እና በርካታ ሀገራት የተኩስ አቁም ጥሪ ቢያቀርቡም ሀማስን ለማጥፋት እቅድ የያዘችው እስራአል ፈቃደኛ አልሆነችም።