የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ እስራኤል በሊባኖስ መሬት ለምትፈጽምው ግድያ “ከባድ ዋጋ ትከፍላለች’ ሲሉ አስጠንቅቀዋል
እስራኤል የሃማስን ምክትል የፖለቲካ መሪ ሳሌህ አል አሩሪ መግደሏ ተነገረ።
የሊባኖስና ፍልስጤም የደህንነት ምንጮቹን ጠቅሶ ሬውተርስ እንደዘገበው የ57 አመቱ አል አሩሪ በሊባኖስ መዲና ቤሩት ነው በድሮን ጥቃት የተገደሉት።
ግድያውን ተከትሎ ለሃማስ አጋርነቱን ያሳየው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስቧል።
ማርጅ በተባለው የድንበር አካባቢ በሰፈሩ የእስራኤል ወታደሮች ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙንም ገልጿል።
የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ እስራኤል በሊባኖስ ምድር ለምትፈጽመው ግድያ “ከባድ ዋጋ ትከፍላለች” ሲሉ ዝተዋል።
እስራኤል በቤሩት የተገደሉትን የሃማስ ምክትል የፖለቲካ መሪ ሳሌህ አል አሩሪ የሃማስን ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ በመመስረት በዌስትባንክ በሚገኙ ዜጎቿ ላይ ጥቃት አድርሷል በሚል ትከሳለች።
ሃማስ በበኩሉ አል አሩሪ በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት ለተደረሰው የጋዛ ተኩስ አቁምና የእስረኛና ታጋች ልውውጥ ቁልፉ የቡድኑ አመራር እንደነበሩ ይገልጻል።
እስራኤል የአል አሩሪን ግድያ ማረጋገጥም ሆነ ማስተባበል አልፈለገችም። የእስራኤል ጥፕር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኔል ሃጋሪም “ዋናው ትኩረታችን ሃማስን መዋጋት ነው” ከማለት ውጭ በቤሩት ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት ማብራሪያ አልሰጡም።
የሄዝቦላህም ሆነ ሃማስ ደጋፊዋ ኢራን የአል አሩሪ ግድያ የፍልስጤማውያንን የነጻነት ትግል ያጠናክረዋል ብላለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ፥ “ግድያው በጺዮናውያን ወራሪዎች ላይ በፍልስጤም የተጀመረውን ትግል ወደ ቀጠናው ያሰፋዋል” ማለታቸው ተዘግቧል።
በራማላህ እና በሌሎች የዌስትባንክ ከተሞች የሚገኙ ፍልስጤማውያንም የአል አሩሪን ግድያ ተቃውመው አደባባይ የወጡ ሲሆን የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የሃማስ ምክትል የፖለቲካ መሪው ሳሌህ አል አሩሪ በቤሩት መገደል የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አድማሱን እያሰፋ ይሄዳል የሚለውን ስጋት አንሮታል።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በትናንትናው እለት ብቻ 207 ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን፥ የሟቾቹ ቁጥር 22 ሺህ 185 ደርሷል።