እስራኤል 700 የሃማስና የኢስላሚክ ጂሃድ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ገለጸች
ባለፈው ሳምንት ብቻ 200 ፍልስጤማውያን ታጣቂዎችን መያዟንም አስታውቃለች
ሃማስ በበኩሉ ቴል አቪቭ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን ሴቶችና ህጻናት እየገደለች ነው ብሏል
እስራኤል ባለፈው ሳምንት 200 የሃማስና የኢስላሚክ ጂሃድ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ገለጸች።
ይህም ከጥቅምት ሰባቱ ጥቃት በኋላ በጋዛ የተያዙ ፍልስጤማውያን ታጣቂዎች ቁጥርን 700 አድርሶታል ብሏል የሀገሪቱ ጦር ባወጣው መግለጫ።
እስራኤል በንጹሃን መኖሪያዎች ውስጥ ተደብቀው የነበሩና እጃቸውን በፈቃዳቸው ሰጥተዋል ያለቻቸውን ታጣቂዎች ወደ ግዛቷ በመውሰድ ምርመራ እያደረገችባቸው እንደምትገኝ አስታውቃለች።
የፍልስጤሙ ሃማስ በበኩሉ እስራኤል በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸው አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውንና እየገደለቻቸው እንደምትገኝ ገልጿል።
ለሃማስ ክስ ምላሽ ያልሰጠችው ቴል አቪቭ በቡድኑ ላይ የምወስደውን እርምጃ እስኪደመሰስ ድረስ እቀጥላለሁ ስትል ዝታለች።
በጋዛ ማዕከላዊ ክፍል የሚኖሩ ከ150 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቧንም የመንግስታቱ ድርጅት ያወጣው መረጃ ያሳያል።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው ድብደባ ከ20 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለው፤ ከ50 ሺህ በላዩ ቢቆስሉም ሃማስን የመደምሰስ ዘመቻዋን የማቆም ምንም አይነት ፍላጎት አላሳየችም።
በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲለቁ የተሰጣቸው አዲስ ማሳሰቢያም ጋዛን ምንም አይነት መሸሸጊያ የሌላት “የምድር ሲኦ” አድርጓታል እየተባለ ነው።
የፍልስጤማውያን ሰቆቃን እጋራለሁ የሚሉት የኔታንያሁ አማካሪ ማርክ ሬጄቭ፥ ለንጹሃን እንግልት ዋነኛው ተጠያቂ “ለህዝቡ ሰላማዊ እስትንፋስ የማይፈቅደው ሃማስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፥ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ጥቃት ሚሊየኖች ሰብአዊ ድጋፎች እንዳይደርሳቸው እያደረገ መሆኑን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
11ኛ ሳምንቱን የያዘውን ጦርነት ለማቆም በኳታርም ሆነ በግብጽ የሚደረጉ ድርድሮች እስካሁን ፍሬ አላፈሩም።