ኔታንያሁ ከጦርነቱ በኋላ ሀማስ ጋዛን አያስተዳድርም አሉ
ኔታንያሁ ይህን የተናገሩት ከእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እና ጦር አዛዥ ጋር በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ ለመገምገም በጋዛ በተገኙበት ወቅት ነው
እስራኤል በጋዛ በህይወት አሉ ተብለው የሚገመቱት 101 ታጋቾች ያሉበትን ቦታ ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኗን ኔታንያሁ ገልጸዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል የሀማስን ወታደራዊ አቅም ለማውደም እያደረገች ያለው ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሀማስ ጋዛን አያስተዳድርም ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ በህይወት አሉ ተብለው የሚገመቱት 101 ታጋቾች ያሉበትን ቦታ ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኗን የገለጹት ኔታንያሁ አንድ ታጋች ለሚያስመልስ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
"የታገቱ ዜጎቻችንን ለመጉዳት የሚደፍር ዋጋውን ያገኛል። አድነን እኒዘዋለን" ብለዋሌ ኔታንያሁ።
ኔታንያሁ ታጋቾችን ይዞ የሚመጣ ማንኛውም ሰው ከእነቤተሰቦቹ ከተከበበችው ጋዛ እንዲወጣ እንደሚመቻችለት ገልጸዋል።
"ምረጥ፤ ምርጫው ያንተ ነው። ነገርግን የኋላ ኋላ ታጋቾቹን ማግኘታችን አይቀርም።"
ኔታንያሁ ይህን የተናገሩት ከእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እና ጦር አዛዥ ጋር በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ ለመገምገም በጋዛ በተገኙበት ወቅት ነው።
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ 1200 ሰዎችን ሲገድል 250 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ ወስዷል። ይህን ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው መጠነሰፊ የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ43ሺ በላይ አልፏል።
በኳታር አደራዳሪነት የተወሰኑ ታጋቾች በፍልስጤማውያን እስረኞች ተለውጠው የተለቀቁ ቢሆንም አብዛኞቹ እስካሁን በሀማስ እጅ እንዳሉ ይታመናል።
በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ኳታር፣ ግብጽ እና አሜሪካ ያደረጉት ጥረት አልተሳከም።
ሀማስ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ጠቅልሎ እንዲወጣ መፈለጉ እና እስራኤል የጋዛን የጸጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ለመቆጣጠር ያላት ፍለጎት ለድርድሩ አለመሳካት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።