የሀማስ ታጣቂዎች በመጀመሪያው ዙር ለተለቀቁ ታጋቾች ያበረከቱት "የስጦታ ቦርሳ" ምን ምን ይዟል?
ለ471 ቀናት በእገታ ላይ የሰነበቱት ሶስት ታጋቾች ከተቁስ አቁም ስምምነቱ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ ተለቀዋል
በአሁኑ ወቅት 95 እስራኤላውን ታጋቾች በሃማስ ታጣቂዎች ስር የሚገኙ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ አራት ታጋቾች እንደሚለቀቁ ይጠበቃል
እስራኤል እና የሃማስ ታጣቂዎች ለ15 ወራት ሲካሄዱት የነበሩትን ውግያ በተኩስ አቁም ለመቋጨት መስማማታቸውን ተከትሎ ተኩስ አቁሙ ከእሁድ ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡
በጥቅምት 7 2023 የሀማስ ጥቃት ወቅት ታግተው ከተወሰዱ 250 ሰዎች መካከል ስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ እስኪጀምር ድረስ በሀማስ እጅ 98 ታጋቾች ይገኙ ነበር፡፡
በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት ታጋቾች እና እስረኞችን መለዋወጥ እሁድ ሲጀመር ፊታቸውን በጭንበል የሸፈኑ የሀማስ ታጣቂዎች ለሶስቱ የእስራኤል ታጋቾች የስጦታ ከረጢት ሲያበረክቱ ታይተዋል፡፡
የቃሳም ብርጌድ አባላት የሆኑት ታጣቂዎች በመጀመሪያ ዙር የተለቀቁትን ሶስት ሴት ታጋቾች ሮሚ ጎነን፣ ዶሮን ስቴይንብሬቸር እና ኤሚሊ ዳማሪ በጋዛ ለቀይ መስቀል ሰራተኞች ባስረከቡበት ወቅት ለእያንዳንዳቸው የቃሳም ብርጌዶች አርማ ያለበት የወረቀት ቦርሳ (የስጦታ ቦርሳ) ሰጥተዋቸዋል።
እስራል “ታጣቂ ቡድኑ ለአመት ያህል ያለፍቃዳቸው አግቶ ይዟቸው ለነበሩ ሰዎች ስጦታ ሰጠሁ ማለቱ ንጹህ ፕሮፖጋንዳ ነው” ስትል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኩል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
በስጦታ ቦርሳው ውስጥ የፍልስጤም ባንዲራ የታተመበት ሀብል፣ የጋዛ ሰርጥን ካርታ የያዘ ምስል እና ታጋቾቹ በእገታ በነበሩበት ወቅት የተነሷቸውን ፎቶዎች እንዳካተተ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ዘገባው ሀማስ በዚህ ድርጊቱ ለእስራኤላውያን፣ ለጋዛውያን እና በዓለም ዙሪያ ለሚመለከቱት ሰዎች ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት በጦርነቱ አለመሸነፉን እና አሁንም ህጋዊ የጋዛ የአስተዳደር አካል መሆኑን ማሳየት ነው ብሏል፡፡
ታጋቾች በተለቀቁበት ወቅት በርካታ የቃሳም ብርጌድ አባላት መታየታቸውን ተከትሎ በጋዛው ጦርነት እስራኤል አሳክቸዋለሁ ያለችው ሀማስን የማጥፋት ኢላማ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር “ሃማስን ማዳከም ብንችልም ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅሙን የማፍረስ ዓላማችንን አላሳካንም” ሲሉ አምነዋል።
የአሜሪካ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው እስራኤል በርካታ የሀማስ ታጣቂዎችን የመደምሰሷን ያህል ቡድኑ በዛው ልክ ብዙ አዳዲስ ታጣቂዎችን መመልመሉን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 95 እስራኤላውን ታጋቾች በሃማስ ታጣቂዎች ስር የሚገኙ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ አራት ታጋቾች እንደሚለቀቁ ይጠበቃል፡፡