እስራኤል በ2024 ለጦርነት 28 ቢሊየን ዶላር ወጪ ማድረጓን አስታወቀች
ለጦርነት የወጣው ገንዘብ የሀገሪቱ እዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ያለው ድርሻ ወደ 69 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል
ቴል አቪቭ በጋዛ፣ ሊባኖስ፣ የመን፣ ኢራን እና ሌሎች ሀገራት ላይ የወሰደቻቸው ወታደራዊ እርምጃዎች ከፍተኛ ወጪን ጠይቀዋል
እስራኤል በ2024 ለጦርነት 100 ቢሊየን ሸክል (28 ቢሊየን ዶላር) ወጪ ማድረጓን ገለጸች።
የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው መረጃ፥ ወታደራዊ ወጪው የመንግስትን የብድር ፍላጎት አሳድጎ የሀገሪቱን የእዳ ጫና ከፍ አድርጓል ብሏል።
የሀገሪቱ እዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ያለው ድርሻ በ2023 ከነበረበት 61.3 በመቶ ወደ 69 በመቶ ከፍ ማለቱንም አስታውቋል።
እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር የምታካሂደው ጦርነት፤ በሊባኖስ በሄዝቦላህ፤ በየመን ደግሞ በሃውቲ ታጣቂዎች ላይ ተከታታይ እርምጃ መውሰዷ ወታደራዊ ወጪዋን ከፍ አድርገውታል።
ከኢራን ጋር ለተሰነዘረባት የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠትና በቴህራንና ቤሩት የሃማስና ሄዝቦላህ መሪዎችን ለመግደል የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸመት ያወጣችው ወጪም ከፍተኛ ነበር።
ባለፉት ሁለት አመታት የእስራኤል እዳ ከጂዲፒዋ ያለው ድርሻ በ9 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።
የእስራኤል የእዳ ከጂዲፒ ንጻሬ ከአውሮፓ ህብረት አባላት አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ነው ብሏል የሀገሪቱ ፋይናንስ ሚኒስቴር።
የአውሮፓ ሀገራት እዳ ከጂዲፒ ያለው ድርሻ በአማካይ 88.1 በመቶ ነው። የአሜሪካ 121 በመቶ፤ የጃፓን ደግሞ 251.2 በመቶ ነው ብሏል ሚኒስቴሩ የአይኤምኤፍ መረጃን ዋቢ አድርጎ በመጥቀስ።
የእስራኤል መንግስት እዳ በ2024 ወደ 1.33 ትሪሊየን ሸክል (371.8 ቢሊየን ዶላር) ከፍ ማለቱ ተጠቁሟል። ይህም በ2023 ከነበረበት በ55 ቢሊየን ዶላር ብልጫ ያሳየ ነው ተብሏል።
እስራኤል የጋዛው ጦርነት በጥቅምት ወር 2023 ከተጀመረ ወዲህ 360 ቢሊየን ሸክል (100 ቢሊየን ዶላር) ብድር ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ አሰባስባለች።
ሀገሪቱ ጠንካራ ኢኮኖሚ እና የካፒታል ገበያ ያላት መሆኗ ብድር በቀላሉ እንድታገኝ እንዳስቻላት ባለሙያዎችን ማንሳታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በ2024 ያጋጠማት የበጀት ጉድለት 6.9 በመቶ መድረሱና ከኮሮና ወረርሽኝ ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ግን የሀገራትን የመበደር አቅም የሚበይኑ ሶስት ተቋማት ደረጃዋን ዝቅ እንዲያደርጉት ምክንያት ሆኗል።
በሊባኖስ ከሄዝቦላህ፤ በጋዛ ከሃማስ ጋር ተኩስ ለማቆም የተደረሰው ስምምነት ሀገሪቱ ለጦርነት የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚቀንሰው ታምኖበታል።