ሃማስ የ4 ታጋቾች አስከሬንን አስረክቧል፤ እስራኤል ከ600 በላይ እስረኞችን መልቀቅ ጀምራለች
እስራኤልና ሃማስ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ የፊታችን ቅዳሜ ይጠናቀቃል

በጋዛ የሚገኙ ቀሪ 59 ታጋቾችን ለማስለቀቅ በዶሃ ሊደረግ የነበረው ድርድር በተደጋጋሚ መራዘሙ ይታወሳል
የፍልስጤሙ ሃማስ በጋዛ ህይወታቸው ያለፈ የአራት እስራኤላውያን ታጋቾችን አስከሬን አስረከበ።
ሽሎሞ መንሱር፣ ኦሃድ ያሃሎሚ፣ ሳቺ ኢዳን እና ኢትዚክ ኤልጋራት የተባሉት ታጋቾች አስከሬን በርግጥም የእነርሱ ለመሆኑ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን እስራኤል አስታውቃለች።
ባለፈው ሳምንት ሃማስ ወደ እስራኤል የላከው የሺሪ ቢባስ አስከሬን የሌላ ሰው ሆኖ መገኘቱን ተከትሎ ነው የዘረመል ምርመራው በእስራኤልና ጋዛ ድንበርና በቴል አቪቭ እየተካሄደ ያለው።
ሃማስ የአራቱን ታጋቾች አስከሬኖች ያስረከበው ህዝብ ሳይሰበሰብና እንደከዚህ ቀደሞቹ የመድረክ ትዕይንት ሳያሳይ ነው። ለዚህም እስራኤል መሰል ዝግጅቶች ከተደረጉ እስረኞችን አለቅም በሚል ማስጠንቀቋ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል የፍልስጤሙ ቡድን ታጋቾችን ሲያስረክብ "የዜጎቼን ክብር ዝቅ የሚያደርግ" ዝግጅት ማካሄድ የለበትም በሚል ባለፈው ሳምንት ልትለቃቸው የነበሩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ሳትፈታ መቆየቷ ይታወሳል።
በግብጽ አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነትም ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከ600 በላይ ፍልስጤማውያን እስረኞችን መፍታት መጀመሯና የተወሰኑትም ዌስትባንክ እና ጋዛ መድረሳቸው ተዘግቧል።
ዛሬ ከሚለቀቁት እስረኞች ውስጥ በጋዛው ጦርነት የተያዙ ከ400 በላይ ፍልስጤማውያን የሚገኙበት ሲሆን፥ በእስራኤል የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩ 50 እስረኞችም ይፈታሉ ተብሏል።
ሃማስ የሚያስተዳድረው የእስረኞች ሚዲያ ቢሮ በጋዛ የሚገኝ ሆስፒታል ፍልስጤማውያኑን እስረኞች ለመቀበል ተዘጋጅቷል ብሏል።
እስራኤልና ሃማስ በጥር ወር መጨረሻ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ የፊታችን ቅዳሜ ይጠናቀቃል።
ለሰባት ሳምንታት በዘለቀው የመጀመሪያ ምዕራፍ ስምምነት ሃማስ 34 በህይወት ያሉ እና 10 የታጋቾች አስከሬን አስረክቧል፤ እስራኤል ደግሞ ዛሬ የምትለቃቸውን ጨምሮ 1700 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
ቀሪዎቹን 59 ታጋቾች ለማስለቀቅ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መራዘም ይኖርበታል።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከመጠናቀቁ በፊት በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ድርድር ማድረግ መጀመር ቢኖርባቸውም በተለያየ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጡ ይቀጥል ዘንድ ሁለቱም አካላት ስምምነቱን ለማራዘም መስማማት ይጠበቅባቸዋል።