ሀማስ የእስራኤልን ፍልስጤማውያን እስረኞችን የመልቀቅ ሂደት ማራዘም ውሳኔ ኮነነ
ሀማስ እስራኤል ታጋቾች የተለቀቁበት መንገድ "አዋራጅ" ነው የሚለውን ክስ በስምምነት የገባችውን ግዴት ላለመፈጸም እንደ ሰበብ እየተጠቀመችበት ነው ብሏል

የእስራኤል እስረኞችን የመልቀቅ ሂደት የማራዘም ውሳኔ የተሰማው ሀማስ በመጀመሪያ ዙር የጋዛ ተኩስ ኡቀም ስምምነት መሰረት ስድስት በህይወት ያሉ ታጋቾችን ከለቀቀ በኋላ ነው
ሀማስ የእስራኤልን ፍልስጤማውያን እስረኞችን የመልቀቅ ሂደት ማራዘም ውሳኔ ኮነነ።
የእስራኤልን ፍልስጤማውያን እስረኞችን መልቀቂያ ጊዜ ማራዘም ውሳኔ የኮነነው ሀማስ ታጋቾች የተለቀቁበት መንገድ "አዋራጅ" ነው የሚባለው ውሸት ነው፤ እስራኤል በመጀመሪያው ዙር የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት የገባችውን ግዴት ላለመፈጸም እንደ ሰበብ እየተጠቀመችበት ነው ብሏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ውሳኔ ሆነ ብሎ ስምምነቱን የመጣስ ሙከራ የሚያንጸባርቅና ግዴታውን ለመፈጸም የማይታመን መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲል የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል ኢዛት ኢል ራሽቅ ባወጣው መግለጫ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል እስራኤል እስረኞቹን የመልቀቅ ሂደት ያዘገየችው ሀማስ የሚጠበቅበትን ቅድመ ሁኔታዎቸ እስከሚያሟላ እንደነበር ገልጻ ነበር። የኔታንያሁ ቢሮ እሁድ እለት ባወጣው መግለጫ "ቀጣይ ታጋቾች አሳፋሪ ስነስርአት ሳይካሄድ መለቀቃቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ" እስራኤል 602 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ሳትለቅ ትቆያለች ብሏል።
የሀማሱ አል ራሽቅ ግን ታጋቾች ሲለቀቁ የሚደረገው ስነስርዓት ሰብአዊና ክብር ያለው ሲሆን "ትክክለኛ ስድብ" እያጋጠማቸው ያለው በመለቀቅ ሂደት ላይ ያሉ ፍልስጤማውያን ናቸው ብሏል።
አልራሽቅ ፍልስጤማውያን እስረኞች በሚለቀቁበት ወቅት እጃቸው እንዲታሰር፣ አይናቸው እንዲሸፈንና ደስታቸውን እንዳይገልጹ እንደሚደረግ ተናግሯል።
ሀማስ ታጋቾችን በሚለቅበት ወቅት በህዝብ ፊት ወደ መድረክ በማውጣት የተሰጣቸውን እንዲናገሩ ያደርጋል። የታጋች አስከሬን የያዙ ሳጥኖችም ህዝብ በተሰበሰበበት ፊት እንዲያልፉ ይደረጋል።
የእስራኤል እስረኞችን የመልቀቅ ሂደት የማራዘም ውሳኔ የተሰማው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ባለፈው ቅዳሜ በመጀመሪያ ዙር የጋዛ ተኩስ ኡቀም ስምምነት መሰረት መለቀቅ ያለባቸውን ስድስት በህይወት ያሉ ታጋቾችን ከለቀቀ በኋላ ነው።
የአራት እስራኤል ታጋቾች አስከሬን በሚቀጥለው ሳምንት ይለቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ሀማስ እና እስራኤል 16 ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት ያስቆመውን በግብጽና ኳታር አደራዳሪነት የተደረሰውን ተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲከሱ ይደመጣሉ።