ሃማስ የአለማችን ቀዳሚው ቱጃር ጋዛን እንዲጎበኙ ጠየቀ
ኤለን መስክ እስራኤል በጋዛ ያደረሰችውን ውድመት እንዲመለከቱና ገለልተኛ አቋም እንዲይዙ ነው ሃማስ ጥሪ ያቀረበው
መስክ በእስራኤል ባደረጉት ጉብኝት በሃማስ ጥቃት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መጎብኘታቸው ይታወሳል
የሃማስ ከፍተኛ መሪ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ በጋዛ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
መስክ በእስራኤል የአየር ድብደባ የፈራረሰችውን ጋዛ እና የፍልስጤማውያንን ሰቆቃ እንዲመለከቱ ነው ኦስማን ሃምዳን የተባሉት የቡድኑ ከፍተኛ መሪ በቤሩት በሰጡት መግለጫ ጥሪ ያቀረቡት።
ቢሊየነሩ ከሰሞኑ በእስራኤል ባደረጉት ቆይታ በጋዛ ድንበር አቅራቢያ ሃማስ ያደረሰውን ጉዳት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መመልከታቸው ይታወሳል።
በዚህ ጉብኝታቸውም በሃምስ ለታገቱ ሰዎች ድምጽ ለመሆንና የጥላቻ ንግግሮች በኤክስ (ትዊተር) እንዳይሰራጩ ለመቆጣጠር ቃል መግባታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ይህም ቴል አቪቭ በጋዛ ላይ የፈጸመችውን አሰቃቂ ጥቃት ችላ ያለ እና ወገንተኝነት የታየበት አስተያየት ነው ያሉ ፍልስጤማውያን ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተደምጧል።
“በ50 ቀናት ከ40 ሺህ ቶን በላይ ፈንጂዎችን በንጹሃን ፍልስጤማውያን ላይ ጥላለች” የሚሉት የሃማስ ከፍተኛ መሪ ኦስማን ሃምዳን፥ አሜሪካ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጤንና የጦር መሳሪያዎችን ከማቅረብ እንድትታቀብ ጠይቀዋል።
የኤክስ ወይንም የቀድሞው ትዊተር ባለቤት ኤለን መስክም በጋዛ ጉብኝት አድርገው ለፍልስጤማውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው የጠየቁት።
የኤለን መስኩ የስፔስ ኤክስ ኩባንያ በስታርሊንክ በኩል በጋዛ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመጀመር ከእስራኤል ጋር በመርህ ደረጃ ተስማምቻለሁ ቢልም ቴል አቪቭ እስካሁን ፈቃድ አልሰጠችውም።
በእስራኤል የአየር ድብደባ የኤሌክትሪክ እና ኢንተርኔት መሰረተልማቶቿ የወደመባት ጋዛ ከመላው አለም ግንኙነቷ ከተቋረጠ ከ40 ቀናት በላይ ተቆጥረዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ሃማስ በሌሎች ታጣቂ ሃይሎች ተይዘዋል ያላቸውን ታጋቾች የሚገኙበትን ስፍራ ለማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረደውም ተነግሯል።