የአለም ጤና ድርጅት በጋዛ ወረርሽኝ ከቦምብ ጥቃት በበለጠ በርካታ ሰዎችን ሊጨርስ ይችላል አለ
በመንግስታቱ ድርጅት መጠለያ ጣቢያዎች በተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች የተያዙ ህጻናት ቁጥርም እያሻቀበ እንደሚገኝ ተገልጿል
ለ48 ስአት የተራዘመው የጋዛ ተኩስ አቁም በዛሬው እለት ይጠናቀቃል
በጋዛ እየተስፋፋ የመጣው ወረርሽኝ ከእስራኤል የቦምብ ጥቃት በበለጠ የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል የአለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።
ተቅማጥ እና የመተንፈሻ አካላት ህመም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ተጨናንቀው በሚኖሩባቸው የመንግስታቱ ድርጅት መጠለያዎች በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑንም ጠቅሷል።
የአምስት አመት እና ከዚያ በላይ ህጻናት ላይ የበረታው የተቅማጥ ወረርሽኝ በህዳር ወር መጀመሪያ ከነበረበት በ100 እጥፍ ጨምሯል ነው ያሉት የድርጅቱ ቃል አቀባይ ዶክተር ማርጋሬት ሃሪስ።
ህጻናቱ ምንም አይነት ህክምና እያገኙ ባለመሆኑም በአጭር ጊዜ ህይወታቸውን ልናጣ እንችላለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
እንደ መንግስታቱ ድርጅት መረጃ እስራኤል የምድር ውጊያ ስታደርግበት በቆየችበት ሰሜናዊ ጋዛ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አምስት ሆስፒታሎች ብቻ ናቸው።
ከነዚህ ሆስፒታሎች ውስጥ የቀዶ ጥገና ህክምና እና ሌሎች ከባድ ህመሞችን ማከም የሚችለው አንድ ሆስፒታል ብቻ ነው።
ለሆስፒታሎቹ ፈጣን ድጋፍ ተደርጎ ወደ ስራ ካልገቡ ከእስራኤል የቦምብ ጥቃት የበለጠ ወረርሽኞች የበርካቶችን ህይወት ይቀጥፋሉ ነው ያሉት የአለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ።
የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጀምስ ኢልደር በጋዛ ባደረጉት ምልከታ ሆስፒታሎች በህጻናት እና በጦርነቱ በቆሰሉ ሰዎች መጨናነቃቸውን ገልጸዋል።
የአለም ጤና ድርጅትም ሆነ ዩኒሴፍ በዚህ ፈታኝ ወቅት ዳግም ጦርነቱን መጀመር የማይታሰብ ነው ብለዋል፤ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተፈረመ እጅግ የከበደ ቀውስ ይከሰታል ሲሉም አሳስበዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን “ግባችን ለማሳካት ሙሉ አቅማችን እንጠቀማለን” በማለት ስምምነቱ ሲጠናቀቅ ጦርነቱ ዳግም እንደሚጀመር ተናግረዋል።
እስራኤልና ሃማስን አደራድራ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ያደረገችው ኳታር በበኩሏ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት ማድረግ መቀጠሏን አስታውቃለች።
ለ48 ስአት የተራዘመው የጋዛ ተኩስ አቁም በዛሬው እለት ይጠናቀቃል።